ቀጥታ፡

በጋምቤላ ክልል አነስተኛ መስኖዎችንና ሌሎች አማራጮችን በመጠቀም ከ49 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ይለማል

ጋምቤላ ፤ ነሐሴ 30/ 2018 (ኢዜአ) ፦ በጋምቤላ ክልል የተለያዩ የውሃ አማራጮችንና አነስተኛ መስኖዎች በመጠቀም ከ49 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ለማልማት ወደ ስራ መገባቱን የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሃብት ልማት ቢሮ አስታወቀ።

የቢሮ ኃላፊው አቶ አንድሮው ቱት ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በክልሉ ያለውን በመስኖ የመልማት አቅም በመጠቀም የምግብ ዋስትናን የማረጋገጥ ስራው በልዩ ትኩረት እየተሰራ ነው።

የውሃ ሸሽ/ እርጥበታማ አፈር/ እና አነስተኛ የመስኖ ልማትን የሚያስተባብር የአመራርና የባለሙያዎች ቡድን የመስክ ስምሪት መደረጉንም ገልፀዋል።

በክልሉ በዝናብ ብቻ ሳይወሰን በዓመት ከሁለት ጊዜ በላይ በመስኖ በማልማት የምግብ ዋስትናን የማረጋገጡን ጉዳይ በዘላቂነት ውጤታማ ለማድረግ እየተሰራ ነው ብለዋል።

በክልሉ 2019 የበጋ መስኖ ልማት የውሃ ሸሽ/እርጥበታማ አፈረን/፣ 15 አነስተኛ የመስኖ ተቋማትን፣ 256 የውሃ መሳቢያ ፓምፖችንና ሌሎች የውሃ አማራጮችን በመጠቀም ከ49 ሺህ 300 ሄክታር በላይ መሬት ለማልማት እየተሰራ ነው ብለዋል።

ከመስኖ ልማቱ ከ2 ነጥብ 1 ሚሊዮን ኩንታል በላይ የሰብል ፣የአትክልትና ፍራፍሬ ምርት ለመሰብስብ መታቀዱንም ተናግረዋል።

በበጋው መስኖ ለማልማት የታቀደው መሬት ከቀዳሚው ዓመት በ15 ሺህ ሄክታር መሬት ብልጫ እንደሚኖረው ኃላፊው ገልፀዋል።

ከመጪው ከጥቅምት ወር ጀምሮ ለሚካሄደው የውሃ ሸሽ/ እርጥበታማ አፈርን/ እና  ሌሎች የመስኖ አማራጮች ለመጠቀም  ንቅናቄ የሚፈጥር የአመራርና የባለሙያዎች ቡድን ወደ ዞኖችና ወረዳዎች መሰማራቱንም ተናግረዋል።

በጋምቤላ ክልል ባሮን ጨምሮ አራት ታላላቅ ወንዞችና ሌሎች የውሃ አማራጮችን በመጠቀም ከ780 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በመስኖ ማልማት የሚያስችል አቅም እንዳለ በጥናት መለየቱም ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም