ቀጥታ፡

የመንግሥት አገልግሎትን ለማዘመን በተወሰዱ የሪፎርም ስራዎች ውጤት ተገኝቷል

ሀረር፤ ነሐሴ 30/2018 (ኢዜአ)፦ የመንግሥት አገልግሎትን ለማዘመን በተወሰዱ የሪፎርም ስራዎች አበረታች ውጤት መገኘቱን የፌደራል ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ኮሚሽነር መኩሪያ ሃይሌ (ዶ/ር) ገለጹ።

የፌደራል ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ዓመታዊ የክልል ጉባዔ በሐረር ከተማ እየተካሄደ ነው።

መኩሪያ ሃይሌ (ዶ/ር) በወቅቱ እንደገለጹት ዘመናዊ ቴክኖሎጂን ከብቁ የሰው ኃይል ጋር በማቀናጀት ውጤታማ የአገልግሎት አሰጣጥ ስራ ማከናወን ተችሏል።

የአገልግሎት ተግዳሮቶችን ለመቅረፍ ዘመናዊ የፖሊሲና ፕሮግራም፣ አዋጅና ደንብ እንዲሁም መመሪያና ስታንዳርድ በመቅረጽ ለተግባራዊነቱ ሲሰራ መቆየቱን ተናግረዋል።

በተለይም የመንግሥት አገልግሎትን ለማዘመን በተወሰዱ የሪፎርም ስራዎች አበረታች ውጤት መመዝገቡን አንስተዋል።

በተለይ በአጭር ጊዜ ውስጥ ተግባራዊ በተደረገው ውጤታማ የሪፎርም እርምጃ ከፌደራል እስከ ክልል ድረስ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎቶችን ወደ ሥራ ማስገባት መቻሉን ለአብነት ጠቅሰዋል።

መሶብ የአንድ ማዕከል ዲጂታል አገልግሎት የተገልጋዮችን እንግልት በመቅረፍ የአገልግሎት እርካታን እያሳደገ መሆኑንም ገልጸዋል።

የተጀመረውን ስራ በዘላቂነትና በውጤታማነት ለማሳደግ የአመራር ቁርጠኝነትና የቴክኖሎጂ ትግበራ ቀጣይነትን ማረጋገጥ ወሳኝ ጉዳይ መሆኑን አስገንዝበዋል።

በቀጣይም የተቋማት አቅም ግንባታን በማጠናከር፣ የሰው ኃይልን ከቴክኖሎጂ ጋር የማብቃት ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።

የሐረሪ ክልል ፐብሊክ ሰርቪስ ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ጆርዳን ይስሃቅ በበኩላቸው በክልሉ በአገልግሎት አሰጣጥና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመቅረፍ ውጤታማ ስራዎች ተከናውነዋል ብለዋል።

በተለይ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ፈጣን፣ ቀልጣፋ፣ ጊዜና ገንዘብ ቆጣቢ አሰራርን መሰረት ያደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል ።

የማህበረሰቡን የአገልግሎት አሰጣጥ ጥያቄ በመመለስ ጥራትና ቅልጥፍናን በመጨመርና የብልሹ አሰራር ችግሮችን በማስቀረት የአገልግሎት እርካታን ማሳደግ እያስቻለ መሆኑን ጠቁመዋል።

መድረኩም የአገልግሎት አሰጣጥ ስርዓቱን ይበልጥ ዘመናዊና ቀልጣፋ ለማድረግ መደላድል የሚፈጥር ነው ብለዋል።

ለሁለት ቀናት በሚቆየው ጉባዔ የፌደራል ሲቪል ሰርቪስና የክልል ቢሮ ኃላፊዎች የተገኙ ሲሆን በፌደራልና በክልሎች 2018 በጀት አመት የስራ አፈጻጸም ሪፖርትና የ2019 እቅድ ላይ በመወያየት አቅጣጫ እንደሚቀመጥ ተመላክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም