ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በሰላም ወዳድ ህዝብና በመንግሥት የተቀናጀ ጥረት ፈተናዎችን በድል እየተወጣች ነው - የሰላም ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 30/2018 (ኢዜአ):- ኢትዮጵያ በሰላም ወዳድ ህዝብና በመንግሥት የተቀናጀ ጥረት ፈተናዎችን በድል እየተወጣች መሆኑን የሰላም ሚኒስቴር ገለጸ።

የሰላም ሚኒስቴር በደብረ ማርቆስ ከተማ ለሰላም ግንባታ የባህላዊ ሃብቶችና ሀገር በቀል ዕውቀቶችን ክልሎች ልምድ የሚለዋወጡበት የምክክር መድረክ እያካሄደ ነው።

በመርሃ ግብሩ ላይ የተለያዩ ክልሎች የጸጥታ ዘርፍ የሥራ ኃላፊዎች፣ የኃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች ታድመዋል።

የሰላም ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ኃላፊ መብራቱ ካሳ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ በህዝቦቿና በመንግሥት የተቀናጀ ጥረት ፈተናዎችን በድል ስትወጣ ቆይታለች።

በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች የተከሰቱ ግጭቶችን በሰላም ወዳድ ህዝብና መንግሥት ጥረት እንዲከሽፉ መደረጋቸውን ገልጸዋል።

የአማራ ክልል ህዝብና ወጣቶችም ወደ መደበኛ ልማት እየተመለሱ መሆኑን ተናግረዋል።

ይህውም የክልሉ መንግሥት፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የኃይማኖት አባቶችና ወጣቶች ለሰላምና ልማት ያደረጉትን ጥረት ያሳያል ብለዋል።

ከዚህም ባለፈ የኃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች የሰላም ጥረት ለድህረ ግጭት የሰላም ግንባታ ብሎም ዘላቂ ልማት መሰረት እንደሚጥል ገልጸዋል።

የአማራ ክልል ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ምክትል ኃላፊ ኮሚሽነር ደጀኔ ልመንህ፤ በክልሉ ዘላቂና አስተማማኝ ሰላም እየተገነባ እንደሚገኝ ብለዋል።

የድህረ ግጭት የሰላም ግንባታ ችግሮችን በውይይት፣ በመተማመንና በመግባባት መፍትሄ ለመስጠት በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

የተለያዩ ክልሎች የሀገር ሽማግሌዎች የኃይማኖት አባቶች እና የጸጥታ ተቋማት ትብብርና ልምድ ልውውጥ ለዘላቂ ሰላም ግንባታ ወሳኝ መሆኑንም ተናግረዋል።

ቀጣይነት ያለው ዘላቂ ሰላም ግንባታ የሁሉንም ትብብር እንደሚጠይቅ ገልጸው፤ ለዚህም ከሀገር ሽማግሌዎች፣ የኃይማኖት አባቶች እና የጸጥታ ተቋማት ጋር በትብብር እየተሰራ ነው ብለዋል።

መሰል መድረኮችም ለዘላቂ ሰላም ግንባታና አብሮነት መጎልበት መሰረት መሆናቸውን ገልጸዋል።

የደብረ ማርቆስ ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ተሾመ ዋለ በበኩላቸው፤ የደብረ ማርቆስ ህዝብ ሰላምና ልማት ወዳድ ህዝብ መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህም በፅንፈኛ ኃይሎች አማካኝነት የተከሰተውን ግጭት ከመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ጋር በመተባበር ከተማዋን ወደ ቀደመ ሰላሟ መመለስ ተችሏል ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት ፅንፈኝነትን በቃህ የሚል ማህበረሰብ ተፈጥሯል ያሉት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው፤ ከተማዋ ሰላሟን አስጠብቃ በልማት ጎዳና ላይ እንደምትገኝ ገልጸዋል።

ህዝቡ በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ድምጹን በመስጠት ለጠንካራ ሀገረ መንግሥት ግንባታ ከፍተኛ ተጋድሎ ማድረጉንም ተናግረዋል።

በከተማዋ የኮሪደር ልማት፣ መሶብ የአንድ ማዕከል የመንግስት አገልግሎት እና ሌሎች የማህበረሰቡን ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጡ ከፍተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎች ወደ ስራ መግባታቸውንም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም