በካፍ ሻምፒዮንስ ሊግ ሲዳማ ቡና ከኤግሎንስ ጋር ይጫወታል - ኢዜአ አማርኛ
በካፍ ሻምፒዮንስ ሊግ ሲዳማ ቡና ከኤግሎንስ ጋር ይጫወታል
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 30/2018 (ኢዜአ):- በ2026/27 የካፍ ሻምፒዮንስ የመጀመሪያ ዙር ቅድመ ማጣሪያ ሲዳማ ቡና ከቻዱ ኤግሎንስ ጋር ዛሬ ጨዋታውን ያደርጋል።
ጨዋታው ከቀኑ 11 ሰዓት ከ30 ላይ በኢድሪስ ዴቢ ኢትኖ ስታዲየም ይካሄዳል።
ሲዳማ ቡና በካፍ ሻምፒዮንስ ሊግ ውድድር ላይ ለመሳተፍ የበቃው የ2018 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሻምፒዮን መሆኑን ተከትሎ ነው።
በ1999 ዓ.ም የተቋቋመው ሲዳማ ቡና በአህጉራዊ መድረክ ሲሳተፍ ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ።
በያሬድ ገመቹ የሚመራው ሲዳማ ቡና ለማጣሪያ ጨዋታው በሃዋሳ ልምምዱን ሲያደርግ ቆይቶ በተያዘው ሳምንት ወደ ስፍራው አቅንቷል።
ቡድኑ ስብስቡን ለማጠናከር በክረምቱ የተጫዋቾች የዝውውር መስኮት አዳዲስ ተጫዋቾችን አስፈርሟል፣ የተጫዋቾችንም ውል አድሷል።
ቢኒያም በላይ፣ ውብሸት ክፍሌ፣ ኤፍሬም ታምራት፣ ይገዙ ቦጋለ እና ዩጋንዳዊው ካሊድ አውቾ ከፈረሙት ተጫዋቾች መካከል ይጠቀሳሉ።
በተጨማሪም ሲዳማ ቡና የአምበሉን ያሬድ ባየህ፣ መስፈን ታፈሰ እና ደስታ ደሙን የመሳሰሉ የቁልፍ ተጫዋቾቹን ውል አራዝሟል።
ተጋጣሚው ኤግሎንስ ባለፈው የውድድር ዓመት ለመጀመሪያ ጊዜ የተካሄደውን የቻድ ፕሪሚየር ሊግን ማሸነፉን ተከትሎ በአህጉራዊ መድረኩ ላይ ይሳተፋል።
ኤግሎንስ በካፍ ሻምፒዮንስ ሊግ ሲሳተፍ የአሁኑ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው። እ.አ.አ በ2015 የተመሰረተው ኤግሎንስ የወቅቱ አሰልጣኝ አማን አዱም ቱኒያ ናቸው።
የሊጉ ምርጥ ተጫዋች ተብሎ የተመረጠው አጥቂው ፋቢየን ጄዳኑም እና ምርጥ ግብ ጠባቂ የተባለው ቢርዌ ማንጋና የቡድኑ ቁልፍ ተጫዋቾች ናቸው።
የሁለቱ ክለቦች የመልስ ጨዋታ መስከረም 3 ቀን 2019 ዓ.ም በድሬዳዋ ስታዲየም ይካሄዳል።
ሲዳማ ቡና በደርሶ መልስ ውጤት ካሸነፈ በሁለተኛው ዙር ማጣሪያ ከሱዳኑ አል ሂላል እና ከብሩንዲው አይግል ኑዋር አሸናፊ ጋር ይጫወታል።