ቀጥታ፡

የሊጉ መሪ ማንችስተር ሲቲ ከኮቨንተሪ ሲቲ ጋር ይጫወታል

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 30/2018 (ኢዜአ):- በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የሶስተኛ ሳምንት የሁለተኛ ቀን ውሎ ሰባት ጨዋታዎች ይደረጋሉ።

በኢትሃድ ስታዲየም ከቀኑ 11 ሰዓት ላይ በሚካሄደው ጨዋታ ማንችስተር ሲቲ አዲስ አዳጊውን ኮቨንተሪ ሲቲ ያስተናግዳል።

ባለሜዳው ማንችስተር ሲቲ በስድስት ነጥብ ሊጉን እየመራ ይገኛል።

በሁለቱ የሊጉ ጨዋታዎች ሽንፈት ያስተናገደው ኮቨንተሪ ሲቲ ያለ ምንም ነጥብ 17ኛ ደረጃን ይዟል።

ክለቦቹ ከዚህ ቀደም 10 ጊዜ በሊጉ ተገናኝተው በተመሳሳይ አራት ጊዜ ድል ቀንቷቸዋል። በቀሪ ሁለት ጨዋታዎች አቻ ተለያይተዋል።

ለመጨረሻ ጊዜ በሊጉ የተገናኙት እ.አ.አ በ2001ነው። በወቅቱ ባደረጉት ጨዋታ አንድ አቻ ተለያይተዋል።

ክለቦቹ ከ25 ዓመታት በኋላ ዳግም በሊጉ ይገናኛሉ።

ማንችስተር ሲቲ ካሸነፈ የሊጉን መሪነት የሚያጠናክር ሲሆን ኮቨንተሪ ሲቲ የመጀመሪያ ድሉን ለማስመዝገብ ይፋለማል።

በሌላኛው መርሐ ግብር ከቀኑ 11 ሰዓት ላይ ኖቲንግሃም ፎረስት ከቶተንሃም ሆትስፐርስ በሲቲ ግራውንድ ስታዲየም ይጫወታሉ።

ኖቲንግሃም ፎረስት በአንድ ነጥብ 14ኛ ደረጃን ይዟል። ተጋጣሚው ቶተንሃም ሆትስፐርስ ያለ ምንም ነጥብ 19ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል።

ሁለቱም ክለቦች በሊጉ የመጀመሪያ ድላቸውን ለማስመዝገብ ይጫወታሉ።

በዝውውር መስኮቱ ከ300 ሚሊዮን ፓውንድ በላይ ያወጣው ቶተንሃም ደካማ ጅማሮ ያሳየ ሲሆን በሊጉ የመጀመሪያ ሶስት ነጥብ ለማግኘት ይፋለማል።

ምሽት 1 ሰዓት ከ30 ላይ ሁል ሲቲ አስቶንቪላን በኤምኬኤም ስታዲየም ጨዋታውን ያከናውናል።

አዲስ አዳጊው ሁል ሲቲ በስድስት ነጥብ ሶስተኛ ደረጃን ይዟል። አስቶንቪላ ያለ ምንም ነጥብ የመጨረሻው 20ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

ሁል ሲቲ በመልካም ጅማሮው ለመቀጠል አስቶንቪላ የመጀመሪያ ድሉን ለማስመዝገብ ይጫወታሉ።

በሌሎች መርሐ ግብሮች ብሬንትፎርድ ከሰንደርላንድ፣ ፉልሃም ከክሪስታል ፓላስ እና ብራይተን ከሊድስ ዩናይትድ በተመሳሳይ 11 ሰዓት ላይ ይጫወታሉ።

ከቀኑ 8 ሰዓት ከ30 ኒውካስትል ዩናይትድ ከቦርንማውዝ በሴንት ጀምስ ፓርክ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያከናውናሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም