ቀጥታ፡

አረንጓዴ አሻራ የአየር ንብረት ለውጥ ተጽእኖን በመከላከል ቁልፍ ሚና እየተጫወተ ነው - የአፍሪካ ህብረት

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 30/2018 (ኢዜአ)፡- የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር የአየር ንብረት ለውጥ ተጽእኖዎችን ለመመከትና ለብዝሃ ህይወት ጥበቃ ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሚገኝ የአፍሪካ ህብረት የዘላቂ ከባቢና ብሉ ኢኮኖሚ ዳይሬክተር ሃርሰን ንያምቤ ገለጹ።

ዳይሬክተሩ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ አረንጓዴ አሻራ ንጹህ አየርን ጨምሮ ሌሎች ስነ-ምህዳራዊ ጥቅሞችን ከማስገኘቱም በላይ፣ የካርበን ልቀትን በመቀነስ የአየር ሙቀት መጨመርን ለመከላከል እንደሚያስችል ተናግረዋል።

የተራቆተ መሬትንና የአካባቢ ስነ ምህዳር እንዲያገግም በማድረግ የአየር ንብረት ለውጥ ጉዳትን ለመከላከል እየተደረገ ባለው ጥረት ውስጥ ወሳኝ ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝ አመልክተዋል።

በጥቅሉ ሲታይ የአረንጓዴ አሻራ በርካታ ሁለገብ ጥቅሞች ያሉት ሀገራዊ ኢኒሼቲቭ መሆኑንም አንስተዋል።

የአፍሪካ ሀገራት በአየር ንብረት ለውጥ መከላከል ተግባራት ላይ የልምድ ልውውጥ ማድረግ እንደሚገባቸው የገለጹት ዳይሬክተሩ፤ በዚህ ረገድም በአካባቢ ጥበቃ ላሉባቸው ተግዳሮቶች መፍትሄ ለማበጀት ከኢትዮጵያ ተሞክሮ መውሰድ እንደሚችሉ ነው የገለጹት።

ኢትዮጵያም ስኬታማ ተሞክሮዎቿን ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት በማካፈል ግንባር ቀደም ሚና መጫወት እንዳለባት ዳይሬክተሩ አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም