ሕገወጡ ሕወሓት ከዘመን ጋር መራመድ የማይችልና ብቻውን የቀረ ስብስብ ነው -ብርጋዴር ጄኔራል ኃይሉ ጎንፋ - ኢዜአ አማርኛ
ሕገወጡ ሕወሓት ከዘመን ጋር መራመድ የማይችልና ብቻውን የቀረ ስብስብ ነው -ብርጋዴር ጄኔራል ኃይሉ ጎንፋ
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 29/2018 (ኢዜአ):- ሕገወጡ ሕወሓት ከዘመን ጋር መራመድ የማይችል ያረጀና ብቻውን የቀረ ስብስብ መሆኑን ብርጋዴር ጄኔራል ኃይሉ ጎንፋ ገለጹ።
ብርጋዴር ጄኔራል ኃይሉ ጎንፋ በሀገር መከላከያ ሠራዊት በተለያዩ የአመራር ደረጃዎች ሀገራቸውን ለበርካታ ዓመታት አገልግለዋል።
ብርጋዴር ጄኔራል ኃይሉ በቀደመው ስርዓት በደረሰባቸው ጫና ምክንያት ተሰደው የቆዩ ሲሆን ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎም ወደ ሀገራቸው በመመለስ ኑሯቸውን ኢትዮጵያ አድርገዋል።
ብርጋዴር ጄኔራል ኃይሉ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፣ ሕገወጡ የሕወሓት ቡድን በአሁኑ ወቅት ዓለም የደረሰበትን የወታደራዊ ሳይንስ ዕድገት መረዳት ያልቻለ፣ የአረጀ አስተሳሰብ የተሸከመ ኋላቀር ስብስብ መሆኑን ተናግረዋል።
ቡድኑ ኋላቀር የጦር መሣሪያ በመያዝ፣ በከንቱ ቅዠት ወደ ሥልጣን እመለሳለሁ ብሎ የሚያልም ኋላቀር ስብስብ መሆኑንም አክለዋል።
እንደ ብርጋዴር ጄኔራል ኃይሉ ገለጻ፣ ቡድኑ የዓለምን ተለዋዋጭ ሁኔታና ዕድገት ባለመረዳት ባለፈው ታሪክ ላይ ተቸክሎ ቀርቷል።
ሕገ-ወጥ ቡድኑ ሕዝቦችን በመከፋፈልና የግጭት ትርክትን በማስተጋባት በሥልጣን ላይ መቆየቱን አስታውሰዋል።
አሁንም የዘመኑን መለወጥ መረዳት ያልቻለው ይህ ቡድን ''ትናንት በኃይልና በሴራ በመታገዝ ወደ ሥልጣን ወጥተናል፤ ዛሬም በመሣሪያ እንመለሳለን'' በሚል የእሳቤ ቅዥት ላይ መሆኑን አብራርትዋል።
ይህም ህገ-ወጥ ቡድኑ ዘመናዊነትን የማያውቅና ጠብመንጃ ላይ የቆመ ኋላቀር ስብስብ መሆኑን በተግባር ያረጋገጠ ስለመሆኑም ተናግረዋል።
አሁን ላይ ኢትዮጵያ በወታደራዊ ሳይንስና ቴክኖሎጂ እጅግ ወደ ዘመናዊ ስርዓት መሸጋገሯን በማብራራት፤ በኋላቀር መሣሪያ እና እሳቤ ወደ ስልጣን ለመምጣት የሚደረግ ከንቱ ቅዥት የትም የማያደርስ ኪሳራ ነው ብለዋል።
የህገ ወጡ ሕወሃት አካሄድ በየትኛውም አካል ተቀባይነት ያጣና ብቻውን የቀረ መሆኑንም በተግባር እያየን ነው ብለዋል።