የኢትዮጵያ ጥንካሬ ከተቋሞቿ ድምር አቅም የሚመነጭ ነው-ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ጥንካሬ ከተቋሞቿ ድምር አቅም የሚመነጭ ነው-ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 29/2018 (ኢዜአ):- የኢትዮጵያ ጥንካሬ ከተቋሞቿ ድምር አቅም የሚመነጭ ነው ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው ኢትዮጵያን በጤና እና በትምህርት እያገለገለ ያለውን የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅን የሥራ እንቅስቃሴ ዛሬ ተመልክተናል ብለዋል።
የሆስፒታሉን ብቻ ሳይሆን የሃገራችንን የጤና ዘርፍ ወደ ከፍተኛ ምዕራፍ የሚያሸጋግረረው አኩቴክ (ACCU-TECH) ዲያግኖስቲክ ላብራቶሪ ለሃገራችን የዘርፉ ልዩ መለያ እና አቅም ነው።
ዘመናዊው ላቦራቶሪ በአንድ ጊዜ በርካታ ሳምፕሎችን ከመቀበሉም በላይ ለተወሰነ ጊዜ ሳምፕሎችን በጥንቃቄ ለማቆየትም የሚያስችል ነው።
በተጨማሪም በትምህርት ተቋሙ የስነተዋልዶ ጤና ልህቀት ማዕከልን፣ ለታካሚ እጅግ ምቹ የሆነውን የካንሰር የጨረር ህክምና ማዕከልን እና የአገልግሎት ነጻ የጥሪ ማዕከሉን ተመልክተናል።
ተቋሙ ከሆስፒታልነት በላይ፣ የሰው ኃይል ልማትን፣ የልዩ ሕክምና አገልግሎትን፣ ምርምርንና ዘመናዊ ቴክኖሎጂን በአንድ ላይ ያቀናጀ ሀገራዊ የጤና ተቋም መሆኑን በጉብኝታችን አረጋግጠናል።
ከመላ ኢትዮጵያ እንዲሁም አህጉራችን አፍሪካ ለሚመጡ ታካሚዎች የኩላሊት፣ የልብ እና መሰል ውስብስብ የጤና እክሎችን በዘመናዊ ቴክኖሎጂና ብቃት ባላቸው ሀኪሞቹ አክሞ በማዳን እያበረከተ ያለው ሥራ፣ ኢትዮጵያ በአፍሪካ የሕክምና ልህቀት ማዕከል እና የሕክምና ቱሪዝም መዳረሻ ለመሆን የጀመረችው ጉዞ ትክክለኛ መስመር ላይ መሆኑን ያሳያል።
ሆስፒታሉ ከሆስፒታል ወደ ጤና ከተማ ከኮሌጅ ወደ ሕክምና እና ጤና ሳይንስ ዩኒቨርሲቲ የሚያደርገውን የልህቀት ጉዞ አጠናክሮ መቀጠል ይገባዋል።
በቀጣይም የላቀ የሕክምና አቅምን፣ ትምህርትንና ምርምርን በማጠናከር ለሌሎች የሀገር ውስጥና አህጉራዊ ተቋማት ምሳሌነቱን አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል።