የአሜሪካና የኢትዮጵያ የደህንነት ስምምነት የአፍሪካ ቀንድን አሸናፊ የሚያደርግ የትብብር ማዕቀፍ ነው -ቲቦር ናጅ - ኢዜአ አማርኛ
የአሜሪካና የኢትዮጵያ የደህንነት ስምምነት የአፍሪካ ቀንድን አሸናፊ የሚያደርግ የትብብር ማዕቀፍ ነው -ቲቦር ናጅ
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 29/2018 (ኢዜአ):- የአሜሪካና የኢትዮጵያ የደህንነት ስምምነት የአፍሪካ ቀንድ ቀጣናን አሸናፊ የሚያደርግ የትብብር ማዕቀፍ መሆኑን የቀድሞው የአሜሪካ አፍሪካ ጉዳዮች ረዳት ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቲቦር ናጅ ገለጹ።
የሀገር መከላከያ ሚኒስቴር የውጭ ግንኙነትና ወታደራዊ ትብብር ዋና ዳይሬክተር ሜጀር ጄኔራል ተሾመ ገመቹ የተመራ ከፍተኛ ወታደራዊ ኃላፊዎችን ያካተተ የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን በቅርቡ በአሜሪካ ጉብኝት በማድረግ በፔንታጎን ከአቻዎቻቸው እና ሌሎች ከፍተኛ የአሜሪካ ጦር ሚኒስቴር አመራሮች ጋር የሁለትዮሽ የጋራ ምክክሮች አድርገዋል።
በዚህም በፔንታጎን የአፍሪካ ጉዳዮች ምክትል ረዳት የመከላከያ ሚኒስትር ብራያን ጄ. ኤሊስ ጋር በጋራ በተመራ ምክክር የሁለቱን ሀገራት ወታደራዊ እና ዲፕሎማሲያዊ ትብብሮችን ወደ አዲስና የላቀ ምዕራፍ ለማሸጋገር ተግባብተዋል።
የቀድሞው የአሜሪካ አፍሪካ ጉዳዮች ረዳት ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቲቦር ናጅ በአሜሪካ እና በኢትዮጵያ መካከል የተጀመረውን ወታደራዊ ትብብር ስትራቴጂካዊ ፋይዳ ያለው መሆኑን ከፐልስ ኦፍ አፍሪካ ጋር ባደረጉት ቆይታ ገልጸዋል።
ከሀገር መከላከያ ሰራዊት ጋር የሚደረግ ትብብር ከሁለቱ ወገኖች አልፎም ለቀጣናው ዘላቂ ሰላም የሚበጅ ውጤት እንደሚያስገኝ ተናግረዋል።
ቲቦር የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ያለውን ከፍተኛ ሙያዊ ብቃት ያደነቁ ሲሆን ይህ ብቃቱ ደግሞ በአፍሪካ ካሉ የፀጥታ ኃይሎች መካከል ቀዳሚ እንደሚያደርገው አመልክተዋል።
የሰራዊቱን ጥንካሬም ከጥልቅ ስነ ምግባር እና ከዘመን ተሻጋሪ ወታደራዊ ታሪክ ጋር አያይዘው አንስተዋል።
የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ያለው ሙያዊ ስነ ምግባር እና ታሪክ ሁልጊዜም በከፍተኛ የሙያ ደረጃ ላይ እንዲቀመጥ አድርጎታል ነው ያሉት።
ይህ ሰራዊት የአድዋን ታሪክ የሰሩ አርበኞችን ጀግንነት የወረሰ ነው ያሉት ናጅ፤ የኢትዮጵያውያን የውጊያ መንፈስ እና ለሀገር የመዋጋት ፍላጎት በደማቸው ውስጥ ያለ መሆኑን አመልክተዋል።
ይህ ተቋማዊ ብቃት አሜሪካ ከኢትዮጵያ ጋር ቀጣይነት ያለው ግንኙነትና አጋርነት ለመፍጠር ላለት ፍላጎት እጅግ የጎላ ፋይዳ እንዳለው አመልክተዋል።
አሜሪካ ጥቅሟቿን ለማስከበር ከመከላከያ ሰራዊት ጋር ትብብር መፍጠሯ እጅግ አስፈላጊ መሆኑን ነው የተናገሩት።
የተረጋጋ እና የበለጸገ የአፍሪካ ቀንድ የአሜሪካን ስትራቴጂካዊ ጥቅሞች እንደሚያስጠብቅም አፅንኦት ሰጥተዋል።
በአጠቃላይ ጥልቅ የሆነው የአሜሪካና ኢትዮጵያ ወታደራዊና ስትራቴጂካዊ ትብብር ሁሉንም ወገኖች አሸናፊ የሚያደርግ መሆኑን ገልጸዋል።