በሲዳማ ክልል የተቋማትን የአገልግሎት አሰጣጥ ማዘመን ቅድሚያ ትኩረት የተሰጠው ተግባር ነው - ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ - ኢዜአ አማርኛ
በሲዳማ ክልል የተቋማትን የአገልግሎት አሰጣጥ ማዘመን ቅድሚያ ትኩረት የተሰጠው ተግባር ነው - ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ
ሀዋሳ፤ ነሐሴ 29/2018 (ኢዜአ) ፦ በሲዳማ ክልል የተቋማትን የአገልግሎት አሰጣጥ ማዘመን በትኩረት የሚከናወን ተግባር መሆኑን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ ገለጹ።
የክልሉ ሥራና ክህሎት ቢሮ የ ISO 9001: 2015 የጥራት ሥራ አመራር ትግበራ ምስክር ወረቀት ማግኘቱን ተከትሎ የእውቅና አሰጣጥ ሥነ-ሥርአት ተካሂዷል።
በሥነ ስርአቱ ላይ የተገኙት ርዕሰ መስተዳድሩ እንደገለጹት በክልሉ የአሰራር ጥራትና ቅልጥፍናን በማላቅ ለዜጎች የተሻለ አገልግሎት እየተሰጠ መሆኑን ገልፀዋል።
በዚህም ህዝቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የተለያዩ የለውጥ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን ገልጸው፣ በተቋማት ውስጥ የአሰራር ሥርዓትን የማዘመን እና ባለሙያዎችን የማብቃት ሥራ ሲከናወን መቆየቱን ጠቁመዋል።
የክልሉ ሥራና ክህሎት ቢሮን ለሥራ ምቹ በማድረግና አገልግሎቱን ቀልጣፋና ዘመናዊ በማድረግ የተቋሙን ተልዕኮ ለማሳካትና ሀገራዊ የሪፎርም ሥራዎችን ዕውን ለማድረግ የሚያስችል ሥራ መስራቱንም ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅትም የተቋማት የአገልግሎት አሰጣጥ እየተሻሻለ መሆኑን ጠቅሰው፣ ቀደም ብለው ወደ ሥራ በገቡ የሲዳማ እና የሀዋሳ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎቶችም የተገልጋይ እርካታን ማረጋገጥ ተችሏል ብለዋል።
የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ነቢሃ መሀመድ በበኩላቸው እንደገለጹት ሚኒስቴሩ ባለፉት አምስት ዓመታት በተቋማት ግንባታ፣ በክህሎት ልማት፣ በሥራ ዕድል ፈጠራ እና በአሰሪና ሠራተኛ ግንኙነት ባከናወናቸው ተግባራት ውጤቶችን አስመዝግቧል።
በተለይ ክህሎት መር የሥራ ዕድል ፈጠራ ተነድፎ ወደ ሥራ ከተገባ በኋላ በርካታ ውጤታማ የሆኑ ወጣቶችን ማፍራት እንደተቻለ ገልጸው፣ በቴክኒክና ሙያ ተቋማት ላይ የነበረውን ተለምዷዊ አሰራርና አስተሳሰብ ወደ ተሻለ እሳቤና ለውጥ ማምጣት ተችሏል ብለዋል።
የሲዳማ ክልል ሥራና ክህሎት ቢሮ የሥራ አካባቢን ምቹ በማድረግ፣ የሰው ኃይል በማብቃትና ዲጂታል አሰራርን በመዘርጋት ውጤታማ ተግባር ማከናወኑን ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ የተስማሚነት ምዘና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር መዓዛ አበራ እንደገለጹት፣ የአገልግሎት አሰጣጥንና የምርት ጥራትን ማረጋገጥ የአመራር ቁርጠኝነትን ይጠይቃል።
ለእዚህም አመራሩ በባለቤትነት መስራትና ባለሙያን የማብቃት ሥራውን ቀጣይነት ባለው መልኩ ማከናወን አለበት ብለዋል
በተቋማት ውስጥ የጥራት ባህልን ማዳበር እንደ ሀገር የተያዙ ግቦችን ለማሳካት ወሳኝ ሚና እንደሚኖረውም ጠቅሰዋል፡፡
ተቋማቸው አምራች ድርጅቶችና አገልግሎት ሰጪ ተቋማትን ኦዲት በማድረግ የጥራት ሰርተፍኬት እንደሚሰጥ ያወሱት ዳይሬክተሯ፣ የሲዳማ ክልል ሥራና ክህሎት ቢሮም ኦዲት ተደርጎ የተቀመጠውን የጥራት መስፈርት አሟልቶ በመገኘቱ የISO 9001: 2015 የምስክር ወረቀት ባለቤት ለመሆን መቻሉን አስረድተዋል፡፡
የክልሉ ሥራና ክህሎት ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ሀገረፅዮን አበበ በቢሮው ባለፉት አምስት ዓመታት ብቁና ተወዳዳሪ ተቋም ለመገንባት በርካታ የሪፎርም ሥራዎችን ማከናወኑን ገልጸዋል።
በአገልግሎት አሰጣጥ የህብረተሰቡን እርካታ ለማረጋገጥ አሰራሮችን የማዘመን፣ ባለሙያዎችን የማብቃትና ሌሎች ሥራዎች ሲከናወኑ መቆየታቸውንም አመልክተዋል።
የISO 9001:2015 የምስክር ወረቀቱም ቢሮው በዘርፉ የተቀመጡ የሪፎርም አቅጣጫዎችን በአግባቡ ለመተግባር ቁልፍ መሳሪያ ሆኖ እንደሚያገለግለው ተናግረዋል።
በዕውቅና አሰጣጥ ሥነ-ሥርዐቱ ላይ የሲዳማ ክልል ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ፋንታዬ ከበደ ፣ በብልፅግና ፓርቲ የሲዳማ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አብርሀም ማርሻሎ እና ሌሎች የክልልና የፌዴራል የሥራ ኃላፊዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል፡፡