የህብረተሰቡን የአስተዳደር የፍትህ ጥያቄዎች በዘላቂነት ለመመለስ የሚያስችል ሥርዓት ተዘርግቷል-ፍትህ ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
የህብረተሰቡን የአስተዳደር የፍትህ ጥያቄዎች በዘላቂነት ለመመለስ የሚያስችል ሥርዓት ተዘርግቷል-ፍትህ ሚኒስቴር
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 29/2018 (ኢዜአ):- ባለፉት ዓመታት የህብረተሰቡን የአስተዳደር የፍትህ ጥያቄዎች በዘላቂነት ለመመለስ የሚያስችል ሥርዓት መዘርጋቱን የፍትህ ሚኒስትር ዴኤታ ኤርሚያስ የማነብርሃን (ዶ/ር) ገለጹ።
የፍትህ ሚኒስቴር የአስተዳደር ፍትሕ እና የአስተዳደር ፍርድ ቤቶች ላይ የሚመክር ሀገራዊ ኮንፍረንስ አካሄዷል።
ፍትህ ሚኒስትር ዴኤታ ኤርሚያስ የማነብርሃን (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ የአስተዳደር ፍትህ ዋና ዓላማ ዜጎች ወደ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት በሚሄዱበት ወቅት መብታቸውን አውቀው የሚደመጡበትና ረክተው የሚመለሱበትን ስርዓት መፍጠር ነው።
በኢትዮጵያ የህግ የበላይነትን በተግባር ለማስፈንና የህዝብን አመኔታ ለማረጋገጥ የአስተዳደር ፍትህ ስርዓት ወሳኝ ሚና እንዳለውም ገልጸዋል።
የህግ የበላይነት ማለት በህግ አሰራር መመራት መሆኑን ጠቁመው፤ ይህንንም በዜጎች የእለት ተዕለት ህይወት ውስጥ በተጨባጭ እውን ለማድረግ የአስተዳደር ፍትህ ትልቅ ሚና እንደሚጫወት አስረድተዋል።
የመንግስትና የህዝብ አስተዳደር ዋነኛ ዓላማ ህጋዊነትን ማስፈንና በህዝብና በመንግስት መካከል ጠንካራ መተማመንን ማጠናከር መሆኑንም ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ የመጣውን ለውጥ ተከትሎ ከተከናወኑ ዋና ዋና የህግ ማሻሻያዎች መካከል የአስተዳደር ፍትህ አንዱ መሆኑን አመላክተው፤ የህብረተሰቡን የአስተዳደር የፍትህ ጥያቄዎች በዘላቂነት ለመመለስ የሚያስችል ስርዓት መዘርጋቱንም አስረድተዋል።
ቀደም ሲል መመሪያዎች ያለ በቂ ቁጥጥር ይወጡ እንደነበርና ያወጣቸው አካል እንኳ ከጊዜ ብዛት ዘንግቷቸው በተሻሩ መመሪያዎች ውሳኔ የመስጠት ችግሮች ይስተዋሉ እንደነበር ጠቁመዋል።
አዲሱ የአስተዳደር ፍትህ ስርዓት ግን በመንግስትና ባለስልጣናት ላይ ግልጽ ተጠያቂነትን በመጣል እነዚህን መሰረታዊ ችግሮች ማቃለል እንዳስቻለ አመልክተዋል።
ህጉ በተግባር ተቋማዊ ህልውና አግኝቶ አገልግሎት ሰጪ አካላት ጠንቅቀው ሊተግበሩት እንደሚገባ አሳስበዋል።
በኢትዮጵያ የጀርመን ኤምባሲ ተወካይ አንጃ ፓውልስ፤ በኢትዮጵያና በጀርመን መካከል ያለው የሁለትዮሽ ግንኙነት በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሠረተና 60 ዓመታት የሚጠጋ ዕድሜ ያለው ነው ብለዋል፡፡
የአስተዳደር ፍትህ የመንግሥት አካላት ሥልጣናቸውን በሕጋዊ መንገድ ብቻ መተገበራቸውን የሚያረጋግጥ በመሆኑ ለመልካም አስተዳደር መሠረታዊ ጉዳይ እንደሆነም አብራርተዋል።
ባለፉት ዓመታት የተገነባውን ጠንካራ ትብብር መሠረት በማድረግ በኢትዮጵያ የአስተዳደር ፍትህን ይበልጥ የሚያጠናክሩ ሥራዎች ላይ አብሮ ለመሥራት ኤምባሲያቸው ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል።
በኮንፈረንሱ በጀርመን መንግስት የልማት ትብብር (GIZ) ድጋፍ በፍትሕ ሚኒስቴር የተዘጋጀ የአስተዳደር ሕግ የስልጠና ሞጁል ርክክብ የተደረገ ሲሆን የአስተዳደር ፍትህ ኮንፈረንሱ ነገን ጨምሮ የሚካሔድ ይሆናል፡፡