ቀጥታ፡

የእንስሳት ኤክስፖርት ገቢን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሳደግ ዘላቂ የአቅርቦት ሰንሰለት መዘርጋት ላይ በትኩረት እየተሰራ ይገኛል

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 29/2018 (ኢዜአ):- የእንስሳት ኤክስፖርት ገቢን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሳደግ ዘላቂ የአቅርቦት ሰንሰለት መዘርጋት ላይ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የእንስሳት ልማት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አስራት ጤራ (ዶ/ር) ገለፁ።

የኤክስፖርት ቄራዎች፣ የሶማሌ ክልል እና የቦረና ዞን የእርድ እንስሳት ነጋዴዎች ማህበር አመራሮች የትስስር ድርድርና የኮንትራት ስምምነት መድረክ እየተካሄደ ነው።

የእንስሳት ልማት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አስራት ጤራ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ ከፍተኛ የእንስሳት ሀብት ያላት ሀገር ብትሆንም ከዘርፉ ማግኘት የሚገባትን የውጭ ምንዛሬ ሳታገኝ ቆይታለች።

በቅርቡ ከተደረጉት የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርሞች እና የምንዛሬ ማሻሻያ ስራዎች ዘርፉን ማሻሻል የሚያስችሉ አዎንታዊ ሁኔታዎች መፈጠራቸውን ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት ከዘርፉ ታገኝ የነበረው ገቢ ወደ 95 ሚሊዮን ዶላር ገደማ እንደነበር ያስታወሱት ዋና ዳይሬክተሩ፣ በ2018 በጀት ዓመት ግን ይህን ገቢ ወደ 128 ነጥብ 3 ሚሊዮን ዶላር ማሳደግ መቻሉን ተናግረዋል።

ሆኖም ሀገሪቱ ካላት አቅም አንጻር ገቢው ከዚህም በላይ መሆን እንዳለበት አብራርተዋል።

በአሁኑ ወቅት በሀገሪቱ የሚገኙ 12 የኤክስፖርት ቄራዎች የማምረት አቅማቸው እስከ 200 ሺህ ቶን የሚደርስ ቢሆንም፣ በየዓመቱ እያመረቱ ያሉት ግን ከአቅማቸው 10 በመቶ ያህሉን ብቻ እንደሆነ ገልጸዋል።

በዚህም በ2019 በጀት ዓመት የቄራዎችን የማምረት አቅም ወደ 50 በመቶ በማሳደግ ስጋና የስጋ ውጤቶችን ወደ ውጭ በመላክ ከ250 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ለማግኘት ማቀዱን አስታውቀዋል።

ይህንን እቅድ ለማሳካት ዋነኛው ማነቆ የሆነውን የእንስሳት አቅርቦት ችግር መፍታት እንደሚገባ የጠቆሙት ዋና ዳይሬክተሩ፤ አርብቶ አደሩን፣ የኤክስፖርት ቄራዎችን እና ሌሎች ባለድርሻ አካላትን ያካተተ አስተማማኝና ዘላቂ የአቅርቦት ሰንሰለት መዘርጋት እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።

ጎን ለጎንም ከዚህ ቀደም በሳውዲ አረቢያ እና በኤምሬትስ ገበያዎች ላይ ብቻ ተወስኖ የነበረውን የስጋ ኤክስፖርት ወደ ሌሎች አዳዲስ ሀገራት ገበያ ለማስፋት ይሰራል ብለዋል።

እንዲሁም ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ካርጎ ጋር በመተባበር የትራንስፖርትና የካርጎ ማነቆዎችን በቅንጅት የመፍታት ስራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

አርብቶ አደሮችና የእንስሳት ነጋዴዎች ማህበራትን በማደራጀት የመደራደር አቅማቸውን ማሳደግ፣ ህገ-ወጥ የኮንትሮባንድ ንግድን መግታት እና ቀጥታ የትስስር ስርዓት መፍጠር የዘርፉን ተወዳዳሪነት የሚያረጋግጥ ዋነኛ መፍትሄ መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም