በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የትምህርት ጥራትንና የተማሪዎችን ውጤት ለማሻሻል የተጀመሩ ሥራዎች ይጠናከራሉ - ርዕሰ መስተዳድር እንደሻው ጣሰው (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የትምህርት ጥራትንና የተማሪዎችን ውጤት ለማሻሻል የተጀመሩ ሥራዎች ይጠናከራሉ - ርዕሰ መስተዳድር እንደሻው ጣሰው (ዶ/ር)
ሆሳዕና፤ ነሐሴ 29/2018 (ኢዜአ) ፦ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በማህበረሰቡ ተሳትፎ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥና የተማሪዎችን ውጤት ለማሻሻል የተጀመሩ ሥራዎች እንደሚጠናከሩ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር) ገለፁ።
"ዘላቂ የትምህርት ጥራት ፤ ለላቀ የመማር ውጤትና ለብልፅግና " በሚል መሪ ሀሳብ የተዘጋጀ ሦስተኛው የትምህርት ሴክተር ጉባኤ ዛሬ በሆሳዕና ከተማ ተካሂዷል።
በጉባኤው ላይ ርዕሰ መስተዳድሩ እንዳሉት የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥና የተማሪዎችን ውጤት ለማሻሻል ማህበረሰቡን በማሳተፍ የተጀመሩ ሥራዎች ይጠናከራሉ።
በክልሉ ጥራቱን የጠበቀ ትምህርት ተደራሽ ለማድረግ ማህበረሰቡን ያሳተፈ ሥራ መሰራቱንና በዚህም ተስፋ ሰጪ ውጤት ለማስመዝገብ መቻሉንም ርዕሰ መስተዳድሩ ተናግረዋል።
ለዚህም በዘንድሮ ሀገራዊና ክልላዊ ፈተና የተማሪዎች ውጤት መሻሻል በማሳየቱ ውጤቱን አጠናክሮ ለማስቀጠል የባለድርሻ አካላት ቅንጅታዊ ሥራ አስፈላጊ መሆኑን ገልፀዋል።
የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር፣ የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪና የትምህርት ቢሮ ሀላፊ አቶ አንተነህ ፈቃዱ በበኩላቸው፣ የመማር ማስተማር ሥራውን በዲጂታል ቴክኖሎጂ ማገዝ የተወዳዳሪነት አቅምን ያሳድጋል ብለዋል።
ለዚህም በተጠናቀቀው የትምህርት ዘመን 61 ነጥብ 4 በመቶ ለሚሆኑ የ12 ክፍል ተማሪዎች ሀገር አቀፍ ፈተናን በዲጂታል ታግዞ በኦን ላይን ለመስጠት መቻሉን ጠቅሰዋል።
በቀጣይ የትምህርት ዘመንም ፈተናውን በኦን ላይን የሚወስዱ ተማሪዎችን ቁጥር ለማሳደግ ትምህርት ቤቶችን በግብዓት የማሟላት ሥራው በልዩ ትኩረት እንደሚመራ ተናግረዋል።
የከምባታ ዞን ትምህርት መምሪያ ሀላፊ አቶ ዳዊት አሹሮ በዞኑ ማህበረሰቡን በማሳተፍ የትምህርት ጥራትን በማረጋገጥ የተማሪዎችን ውጤት ለማሻሻል በተሰሩ ሥራዎች አበረታች ውጤት መመዝገቡን አንስተዋል።
በተያዘው የትምህርት ዘመንም በትምህርት ለትውልድ ንቅናቄና በትምህርት ቤት ምገባ ማህበረሰቡን በማሳተፍ ውጤቱን አጠናክሮ ለማስቀጠል ወደ ተግባር ተገብቷል ብለዋል።
በህብረተሰቡ ተሳትፎም ስምንት አዳዲስ የቅድመ አንደኛ ትምህርት ቤቶች ተገንብተው ለትምህርት ዘመኑ ዝግጁ መደረጋቸውን አመልክተዋል።
በመርሐ ግብሩ ላይ በክልሉ በዘንድሮ ብሔራዊና ክልላዊ ፈተናዎች ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገቡ ተማሪዎች የማበረታቻ ሽልማትና እውቅና ተሰጥቷል፡፡
ሽልማትና እውቅና ከተሰጣቸው መካከል በሆሳዕና ከተማ የሊች ጎጎ አዳሪ ልህቀት ትምህርት ቤት ተማሪ ሮቤል ጌታቸው በ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና 590 ነጥብ 08 በማምጣቱ ሽልማትና እውቅና ተሰጥቶታል።
የተሰጠው ሽልማትና እውቅናም በቀጣይ በዩኒቨርሲቲ ቆይታው ጠንክሮ በመማር ውጤታማነቱን ለማስቀጠል መነቃቃት እንደፈጠረለት ተናግሯል።