ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎቱን ቀልጣፋና ተደራሽ ለማድረግ በዲጂታል ቴክኖሎጂ እያዘመነ ነው - ኢንጂነር አብዱልበር ሸምሱ

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 29/2018 (ኢዜአ):- የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎቱን ፈጣን፣ ቀልጣፋና ተደራሽ ለማድረግ በዲጂታል ቴክኖሎጂ እያዘመነ መሆኑን የድርጅቱ ዋና ስራ አስፈጻሚ ኢንጂነር አብዱልበር ሸምሱ ገለጹ።

የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ደንበኞች በዘመናዊ ዲጂታል አማራጭ የሚገለገሉበት የዲጂታል መተግበሪያ ዛሬ አስመረቋል።

የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አብዱልበር ሸምሱ (ኢ/ር) በዚሁ ወቅት፤ ኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ዕድገት የሚያሳልጥ የባሕር ላይ የትራንስፖርት አገልግሎት እየተሰጠ ነው ብለዋል።

በዚህም የዲጂታል ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ለሀገሪቱ የሎጂስቲክስ ዘርፍ አዲስ ምዕራፍ የሚከፍት አሰራር እየተገበረ መሆኑን ተናግረዋል።

ተቋሙ ለአፍሪካ ብቸኛ እና ታሪካዊ የባህር ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪ ሆኖ መቆየቱን ገልጸው፤ በአሁኑ ወቅትም ዓለም አቀፍ ደረጃን የሚመጥን አዲስ አሰራር ስርዓት እየተገበረ ይገኛል ብለዋል።

ዛሬ የተመረቀው ዲጂታል ቴክኖሎጂ ደንበኞች እንግልት በመቀነስ ረገድ ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረው እንዲሁም የኢኮኖሚ እንቅስቃሴውን የሚያፋጥን እንደሆነ አስታውቀዋል።

በቀጣዮቹ ዓመታት ውስጥ ሙሉ ለሙሉ የሚጠናቀቁ ትላልቅ አዳዲስ ሲስተሞች እየተገነቡ መሆኑን ጨምረው አስታውቀዋል።

በዲጂታል ቴክኖሎጂ ዘርፍ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ተቋሙን ከዓለም አቀፍ አሰራሮች ጋር እኩል የሚያሰልፉ መሆኑን ተናግረዋል።


የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ የቦርድ አባልና የኢትዮ-ጂቡቲ ባቡር ትራንስፖርት አክሲዮን ማህበር ዋና ስራ አስፈጻሚ ኢንጂነር ታከለ ኡማ በበኩላቸው ፤ የሎጂስቲክስ ሥርዓቱን የሚያዘምን ሥራ እየተከናወነ መሆኑን አስታውቀዋል።

በዚህም መንግሥት የየብስ ትራንስፖርት፣ የባቡርና የደረቅ ወደብ መሠረተ ልማቶችን ከመገንባት ባለፈ፣ የመርከቦች ቁጥር እንዲበራከት እያደረገ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያን የሎጂስቲክስ አቅም ለማጎልበት ከሚደረጉ ኢንቨስትመንቶች በተጨማሪም የባሕር በር ባለቤትነት ምላሽ ለማረጋገጥ በዋና አጀንዳነት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ዛሬ የተመረቀው ዲጂታል ቴክኖሎጂም አገልግሎቱን ይበልጥ ለማሳለጥ ትልቅ ጥቅም እንደሚሰጥ አስታውቀዋል።

የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ቅልጥፍናን ለማሳለጥ የቴክኖሎጂ አሠራር ወሳኝ መሆናቸውን የተናገሩት ደግሞ የኢትዮጵያ ማሪታይም ባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ፍራሆል ጣፋ ናቸው።

የኢትዮጵያ ዲጂታል 2030 ስትራቴጂንና የሎጂስቲክስ ዘርፍ ስትራቴጂን መሠረት በማድረግ የሎጂስቲክስ ዘርፉን ለማዘመንና አሠራሩን ዲጂታላይዝ የሚያደርጉ በርካታ ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።

የዲጂታል መተግበሪያውም ግልጽ፣ ፈጣንና ዘመናዊ አሠራር ሥርዓትን ለመገንባት የሚያስችል ወሳኝ እርምጃ መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም