የመንግሥት አገልግሎትና አስተዳደር ሪፎርም ተወዳዳሪ ተቋማትና ሠራተኞችን ለማፍራት እያገዘ ነው - መኩሪያ ኃይሌ (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
የመንግሥት አገልግሎትና አስተዳደር ሪፎርም ተወዳዳሪ ተቋማትና ሠራተኞችን ለማፍራት እያገዘ ነው - መኩሪያ ኃይሌ (ዶ/ር)
ድሬዳዋ፤ ነሐሴ 29/2018 (ኢዜአ) ፦ የመንግሥት አገልግሎትና አስተዳደር ሪፎርም ተወዳዳሪ ተቋማትና ሠራተኞችን ለማፍራት ማገዙን የፌዴራል ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ኮሚሽነር መኩሪያ ኃይሌ (ዶ/ር) ገለጹ።
በድሬዳዋ የመንግስት አገልግሎትና አስተዳደራዊ ሪፎርምን ወደ ተግባር ማሻገርን የተመለከተ ውይይት ዛሬ ተካሂዷል።
በውይይቱ ላይ ኮሚሽነሩ እንደገለጹት፤ የመንግስት አገልግሎትና አስተዳደር ሪፎርምን ውጤታማ ለማድረግ ለሰው ሀይል ልማት ከተሰጠው ትኩረት በተጨማሪ ተቋማት በዲጂታል የታገዘ ሥራ እንዲሰሩ እየተደረገ ነው።
ይህም ተወዳዳሪ ተቋማትና ሠራተኞችን በማፍራቱ የመንግሥት አገልግሎቶችን ቀልጣፋና ውጤታማ በማድረግ የህዝብ እርካታን ለማረጋገጥ ማገዙን አስረድተዋል።
የመንግሥት አገልግሎቶችን ቀልጣፋ ለማድረግ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን ተደራሽ ማድረግ ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
የመንግሥት አገልግሎት እና አስተዳደር ሁለንተናዊ ዕድገትን ለማረጋገጥ ወሳኝ ሚና እንዳለው የተናገሩት ደግሞ የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃር ናቸው።
ለዚህም በቴክኖሎጂ የተደገፉ አሰራሮችን የማስፋትና ተቋማትን ለአገልግሎቶች አሰጣጥ ምቹ ማድረግ ላይ አተኩሮ መሰራቱን አንስተዋል።
ለአብነትም ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎትን ለህዝብ ለማድረስ በድሬ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት 15 ተቋማትን በማቀፍ 103 አገልግሎቶችን በመስጠት የተገልጋይን እርካታን ማረጋገጥ መቻሉን አንስተዋል ።
በቀጣይ ድሬ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን በሁሉም አካባቢዎች ተደራሽ በማድረግ ሪፎርሙን ለማሳካት ርብርቡ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
የመንግስት አገልግሎት አሰጣጥን በላቀ ጥራትና በተናበበ መንገድ ለማስቀጠል ሪፎርሙ አዲስ ምዕራፍ መክፈቱን የገለጹት ደግሞ የድሬዳዋ አስተዳደር ፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሃብት አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ አቶ ሐይር ሐጂ ኑር ናቸው።
ሪፎርሙ በህዝብ የአገልግሎቶች ላይ እርካታን በማረጋገጥ ውጤታማ አስተዳደር ለማስፈን ያስችላል ብለዋል።