ኢንስቲትዩቱ የሀገሪቱን የልማት ጉዞ የሚያፋጥን የሰው ሃይል የማፍራት ድርሻውን ያጠናክራል - ኢዜአ አማርኛ
ኢንስቲትዩቱ የሀገሪቱን የልማት ጉዞ የሚያፋጥን የሰው ሃይል የማፍራት ድርሻውን ያጠናክራል
ሃዋሳ ፤ነሐሴ 29/2018 (ኢዜአ) ፡-የፌደራል ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኢንስቲትዩት ገበያ መር አዳዲስ ፕሮግራሞች በመክፈት የሀገሪቱን የልማት ጉዞ የሚያፋጥን የሰው ሃይል የማፍራት ድርሻውን እንደሚያጠናክር አስታወቀ።
ኢንስቲትዩቱ በ2018 በጀት አመት አፈጻጸምና በቀጣይ እቅዶችና አቅጣጫዎች ላይ በሃዋሳ መክሯል።
የፌደራል ቴክኒክና ሙያ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ብሩክ ከድር (ዶ/ር) በወቅቱ እንደገለጹት ኢንስቲትዩቱ ገበያ መር የሆኑ 11 አዳዲስ ፕሮግራሞችን በመክፈትና የተማሪዎች የቅበላ አቅሙን በማሳደግ የሀገሪቱን የልማት ጉዞ የሚያፋጥን የሰው ሃይል በማፍራት የበኩሉን እየተወጣ ነው ።
ለዚህም አቅርቦት መር የነበረውን የስልጠና ሂደት ወደ ፍላጎት መር በመቀየር ዘመኑን የዋጁ የስልጠና ፕሮግራሞች ላይ እየተሰራ ነው ብለዋል።
በሳይበር ሴኩሪቲ፣ በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስና በባዮ ሜዲካል ቴክኖሎጂ ጥናትን መሰረት በማድረግ የስልጠና ዘርፎች መከፈታቸውን ለአብነት ጠቅሰዋል።
ኢንስቲትዩቱ የጥናትና ምርምር፣ የቴክኖሎጂ ሽግግርና ኢንተርፕራይዝ ልማት ተግባራቱን ለማሳካት ከ17ዐ በላይ ኢንዱስትሪዎች ጋር ትስስር መፈጠሩንም አመልክተዋል።
በበጀት አመቱም ከ40 በላይ የምርምር ስራዎችን በማድረግ ለፖሊሲ ግብአትና ለቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲያግዙ እንዲሁም ተኪ ምርቶችን ለማምረት አቅም የመፍጠር ስራ መሰራቱን ጠቁመዋል።
በቀጣይም በኢንስቲትዩቱ የ10 አመት ስትራቴጂክ እቅድ ላይ መሰረት በማድረግ የቴክኒክና ሙያ ተቋማትን ችግር ፈቺ የፈጠራ ማእከላት የማድረጉ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አስታውቀዋል።
በምክትል ከንቲባ ማእረግ የሃዋሳ ከተማ አስተዳደር የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን መምሪያ ሃላፊ አቶ ቸርነት ፍላቴ በበኩላቸው በከተማው በተከናወኑ በርካታ የመሰረተ ልማት ስራዎች የቴክኒክና ሙያ ተቋማትና ባለሙያዎች በፈጠራ ስራ ጉልህ ድርሻ አበርክተዋል ብለዋል።
የቴክኒክና ሙያ ተቋማት ያወጧቸው የሰው ሀይልና የምርምር ስራዎች በከተማዋ እድገት የራሳቸውን ድርሻ ማበርከታቸውን ጠቁመዋል።
ከመድረኩ ተሳታፊዎች መካከል በኢንስቲትዩቱ የቴክስታይልና አፓሬል ፋሽን ቴክኖሎጂ ፋካሊቲ ዲን መረርቱ ዋቁማ (ዶ/ር) እንደገለፁት ኢንዱስትሪው የሚፈልገውን የሰው ሃይል ለማፍራት በመደበኛና በአጫጭር ስልጠናዎች በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል።
ፋሽን ቴክኖሎጂው የሚፈልገውንና ዘመኑን የዋጁ ፕሮግራሞችን በመክፈት የተጀመሩ ስራዎችን በማጠናከር ከዘርፉ የሚገኙ ጥቅሞችን የማሳደጉ ስራ እንደሚጠናከር አመላክተዋል ።
በመድረኩ በቀረቡ የውይይት መነሻ ሰነዶችና የተቋሙ የ10 አመት ስትራቴጂክ እቅድ ላይ ውይይት ተደርጓል።