ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በሰው ሰራሽ አስተውሎት ለአፍሪካ ሀገራት አቅም የሚሆን ውጤታማ ተግባራት እያከናወነች ነው

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 29/2018 (ኢዜአ):- ኢትዮጵያ በሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) ቴክኖሎጂ ለቀጣናው ብሎም ለአፍሪካ ሀገራት አቅም የሚሆን ውጤታማ ተግባራት እያከናወነች መሆኗን የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን (ኢጋድ) ዋና ፀሐፊ ወርቅነህ ገበየሁ(ዶ/ር) ገለጹ።

ዛሬ ነሐሴ 29 ቀን 2018 ዓ.ም ጨምሮ ለሁለት ቀናት የሚቆየው የኢጋድ አባል ሀገራት ተወካዮችና ባለድርሻ አካላት የተሳተፉበት፣ የቀጣናውን የሰው ሰራሽ አስተውሎት ስትራቴጂ በጋራ ለመቅረጽ ያለመ አውደ ጥናት መካሄድ ጀምሯል።


 

የኢጋድ ዋና ፀሐፊ ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ የሰው ሰራሽ አስተውሎት ፈጣን ዕድገት የዓለም ኢኮኖሚን፣ መንግሥታትንና የሰውን አቅም እየቀረጸ ይገኛል። 

የሰው ሰራሽ አስተውሎት እና የዲጂታል ዘርፍ የቀጣናዊ የኢኮኖሚ ውህደትን በማፋጠን ለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ወሳኝ ኃይል መሆኑንም ገልጸዋል። 

የምስራቅ አፍሪካ ልማት በይነ-መንግሥታት ባለሥልጣን (ኢጋድ) አባል ሀገራትም የሰው ሰራሽ አስተውሎት የቴክኖሎጂ አማራጭን በአግባቡ በመጠቀም የኢኮኖሚ ውህደትን ማፋጠን እንዳለባቸው ተናግረዋል። 

ለዚህም የሰው ሰራሽ አስተውሎት አጠቃቀም እና የመረጃ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ፣ ከአባል ሀገራት ብሔራዊ የሕግ ማዕቀፎች ጋር የተጣጣመ ቀጣናዊ የጋራ ቁጥጥር ሥርዓት መዘርጋት እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።

አፍሪካ የሰው ሰራሽ አስተውሎትና የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ተጠቃሚነት ደረጃ ዝቅተኛ መሆኑን አንስተው፤ ዘርፉ በፍጥነት ለውጥ እያስመዘገበ ያለ መሆኑን ተናግረዋል። 

ስለሆነም ሀገራት ይህ ተግባር የህልውና ጉዳይ መሆኑን በመገንዘብ ሊሰሩ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

ኢትዮጵያ በቀጣናው ብሎም በአፍሪካ ደረጃ በሰው ሰራሽ አስተውሎትና ቴክኖሎጂ  የተሻለ እየሰራች መሆኑንም ጠቁመዋል።

ኤ አይ ዩኒቨርሲቲን ጨምሮ ዘርፉን ለመምራት ኢንስቲትዩት በማቋቋም አበረታች ስራዎችን እያከናወነች መሆኑን ተናግረዋል።  

ዩኒቨርሲቲው ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለቀጣናው ብሎም ለአፍሪካ የሚጠቅም መሆኑንም አብራርተዋል።

የኢጋድ አባል ሀገራቱ የተናበበ ፖሊሲ እንዲኖራቸውና የተሻሉ ተሞክሮዎችን ለማስፋት እየሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።

በቀጣይ ከቀጣናው የተውጣጡ ወጣቶችን የሚያሰለጥን የልህቀት ማዕከል ለማቋቋም እየተሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል።


 

በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የኢጋድ ጉዳዮች ዳይሬክተር ከተማ ኃይሌ በበኩላቸው፤ ሰው ሰራሽ አስተውሎት የኢኮኖሚ እድገትን የሚያፋጥን ብዝኅ ምርታማነት አቅም መገንቢያ እየሆነ መምጣቱን ገልጸዋል።  

በዚህም ሰው ሰራሽ አስተውሎትን ለቀጣናዊ ትብብር፣ ለጠንካራ የፖሊሲ ማዕቀፍ ዝግጅት፣ ለዲጂታል መሠረተ ልማት፣ እንዲሁም ለጥናትና ፈጠራ ኢንቨስትመንት መጠቀም እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።

ኢትዮጵያ በሀገራዊ እና ቀጣናዊ ልማት ውስጥ የዲጂታል ቴክኖሎጂዎችና የሰው ሰራሽ አስተውሎትን ሚና በመገንዘብ ከኢጋድ አባል ሀገራት ጋር በትብብር ለመስራት ቁርጠኛ መሆኗን ተናግረዋል። 

በኢትዮጵያ እየተገነባ ያለው የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ዩኒቨርሲቲም የኢጋድ አባል ሀገራትን እና አጠቃላይ አፍሪካን የሚጠቅም እንደሚሆን ገልጸዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም