የሸገር ከተማ አስተዳደር የሕዝቡን ባህል፣ እሴትና ማንነት ለማሳደግ አልሞ እየሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የሸገር ከተማ አስተዳደር የሕዝቡን ባህል፣ እሴትና ማንነት ለማሳደግ አልሞ እየሰራ ነው
ሸገር ፤ ነሐሴ 29/2018 (ኢዜአ)፦ የሸገር ከተማ አስተዳደር የሕዝቡን ባህል፣ እሴትና ማንነት ለማሳደግ አልሞ እየሰራ እንደሚገኝ የከተማው ከንቲባ ተሾመ አዱኛ (ዶ/ር) አስታወቁ።
በኦሮሞ ባህል ዘንድ የክረምቱን መውጣትና የፀደይ መባቻን ለማብሰር ከሚከወኑት ባህላዊ ክዋኔዎች መካከል የጎቤና ሽኖዬ ጨዋታ አንዱ ነው።
ጎቤ በወጣት ወንዶች የሚከወን፣ ጀግንነትን፣ ፍቅርን፣ ድልን እና የላቀ ተስፋን የሚያንጸባርቅ ባህላዊ ጨዋታ ሲሆን፤ ወጣቶቹ በቡድን ሆነው በድምቀትና በመስመር እርምጃ እየጨፈሩ የዘመኑን መለወጥ የሚያበስሩበት ነው።
ሽኖዬ ደግሞ በወጣት ሴቶች የሚከወን፣ የዋህነትን፣ ውበትን፣ ሰላምን እና አዲስ ተስፋን የሚያበስር ውብ ባህላዊ ጨዋታ ሲሆን፤ ልጃገረዶቹ በባህላዊ አልባሳት አጊጠው፣ የሚከውኑት በደስታ እና በፈገግታ የታጀበ የውበት እና የህብረት ጨዋታ ነው።
በሸገር ከተማ ደረጃ ላለፉት ሳምንታት ሲከወን የቆየው የጎቤና ሺኖዬ ጨዋታ የማጠናቀቂያ መርሃ ግብሩ በፌስቲቫል ትርኢት የሸገር ከተማ ክፍለ ከተሞች ወጣቶችን በማሳተፍ ዛሬ በሰበታ ክፍለ ከተማ ተካሄዷል።
በመርሃ ግብሩ የተገኙት የከተማው ከንቲባ ተሾመ አዱኛ (ዶ/ር)፤ የሸገር ከተማ አስተዳደር ከተመሰረተበት ጊዜ ጀምሮ የኦሮሞን ባህል፣ እሴትና ማንነት ለማሳደግ እየሰራ መሆኑን ገልጸው፣ ይህም ለኢኮኖሚ እድገትና ለአንድነት መጎልበት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው ተናግረዋል።
ባለፉት ሶስት ዓመታት በከተማው በተከናወኑት ተግባራት የባህል ህዳሴን በማጠናከር ለቱሪዝም ምቹ ሁኔታን መፍጠር የተቻለ ሲሆን፣ በዚህም የሕዝቡን ባህል ወደ ላቀ ደረጃ ማሸጋገር ተችሏል ብለዋል።
ወጣቶች በዚህ ፕሮግራም የሕዝቡን ባህልና ማንነት ለማሳየት ከሚያደርጉት እንቅስቃሴ ጎን ለጎን ለሚቀጥለው ትውልድ ለማስተላለፍ እንዲሁም በኦሮሚያ ደረጃ የሚካሄደውን ትርኢት ስኬታማ ለማድረግ መስራት እንዳለባቸው ከንቲባው አሳስበዋል።
የሸገር ከተማ ምክትል ከንቲባና የኢኮኖሚ ክላስተር አስተባባሪ አቶ ጉዮ ገልገሎ በበኩላቸው፤ ሸገር ከተማ የኦሮሞ ሕዝብ ባህል፣ እሴት፣ ማንነት ማሳያ ከተማ መሆኑን ገልጸው፣ ይህ ጨዋታ ዘንድሮ አገራዊ ድሎች በተመዘገቡበት ወቅት መካሄዱ ልዩ እንደሚያደርገው ተናግረዋል።
በከተማው የኦሮሞን ሕዝብ ባህል፣ እሴትና ማንነት የበለጠ በማሳደግና በማስተዋወቅ ለቱሪዝም መስህብነት ለማሳደግ እየተሰራ እንደሚገኝም አቶ ጉዮ ገልጸዋል።