ቀጥታ፡

የሕብረተሰብን ጤና መጠበቅ ለዘላቂ ሀገራዊ ብልጽግና መሠረት ነው -ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 29/2018 (ኢዜአ):- የሕብረተሰብን ጤና መጠበቅ ለዘላቂ ሀገራዊ ብልጽግና መሠረት ነው ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መረጃ የሕብረተሰብ ጤና ድምር ውጤቱ በተሰማራበት ዘርፍ ሁሉ ውጤታማ ተግባር የሚከውን እና ለሀገሩ ሁለንተናዊ ብልፅግና የሚተጋ አምራች ሕብረተሰብ መገንባት ነው ብለዋል።


 

ኢትዮጵያን ላለፉት 100 ዓመታት ያገለገለውን፣ ታሪካዊ ወረት እና ዘመናዊ አቅምን ያጣመረውን የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩትን የሥራ እንቅስቃሴ ዛሬ መመልከታቸውን ገልጸዋል።

የሕብረተሰብን ጤና መጠበቅ ለዘላቂ ሀገራዊ ብልጽግና መሠረት ነው። ተቋሙም በወረርሽኝ ልየታ፣ በበሽታ ክትትልና ምላሽ፣ በላብራቶሪ፣ በምርምር፣ በዲጂታላይዜሽን እና በጤና ስጋት ዝግጁነት የሀገሪቱን የጤና ሥርዓት በጥንካሬ እየደገፈ ይገኛል ነው ያሉት።

በክልሎች የድንገተኛ ሕብረተሰብ ጤና አደጋ መከላከያና መቆጣጠሪያ ማዕከላትን ማቋቋሙና የሪፈራል ላብራቶሪዎችን ማስፋፋቱ የሀገሪቱን የጤና ዝግጁነት አቅም እያጠናከረ ያለ ወሳኝ ተግባር ነው ብለዋል።

በቀጣይም የአፍሪካ የሕብረተሰብ ጤና የልህቀት ማዕከል ለመሆን በከፍተኛ ትጋት እየሠራ ይገኛል። ከዚህ በተጨማሪም የዓለም የጤና ድርጅት የትብብር ማዕከል በመሆን ዓለም አቀፍ ሚናውን ለማጠናከር ብርቱ ጥረት እያደረገ ነው ሲሉም ገልጸዋል።


 

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደገለጹት የትላንትን ታሪክ ጠብቆ፣ ዛሬን በዘመናዊነት ዋጅቶ፣ ወደ ነገ የሚገሰግስ እንደዚህ ያለ ተቋምን መደገፍና ማጠናከር ለነገ የማንለው ተግባር ነው።

ኢንስቲትዩቱ የሀገርን ብልፅግና ለማፋጠን ወሳኝ አቅም በመሆኑ መንግሥት አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም