የህዳሴ ግድብን ያሳካው ትውልድ የባህር በር ጥያቄንም ማሳካቱ የማይቀር ነው - ኢዜአ አማርኛ
የህዳሴ ግድብን ያሳካው ትውልድ የባህር በር ጥያቄንም ማሳካቱ የማይቀር ነው
ሰቆጣ፤ ነሃሴ 29/2018(ኢዜአ) ፦ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን በመገንባት ታሪክ የሰራው ትውልድ የባህር በር ባለቤትነትን ማሳካቱ የማይቀር ነው ሲሉ የቀድሞ የመከላከያ ሰራዊት መኮንኖች ገለጹ።
ኢትዮጵያዊያን በራሳቸው የፋይናንስ አቅምና ጉልበት ለዓመታት በጽናት የገነቡት የህዳሴ ግድብ ተጠናቆ ኃይል እያመነጨ፣ ዓሳ እየተመረተበት እና የአካባቢውን መልካዐ ምድር አስውቦ የቱሪስት መስህብ ጭምር ሆኗል።
የዚህ ታሪካዊ ስኬት ባለቤት የሆነው የአሁኑ ትውልድ በሁሉም ረገድ የኢትዮጵያን ስኬት፣ ክብርና ልእልና ለማስጠበቅ በትጋት መስራቱን ቀጥሏል።
በቅርበትም፣ በመልክዐ ምድርም ይሁን በታሪክ በቀይ ባህር ላይ የባህር በር ባለቤትነቷን እውን ማድረግ የትውልዱ ጥያቄ ሆኖ ቀጥሏል።
ከአስተያየት ሰጪዎቹ መካከል ሻለቃ ባሻ ሞገስ የማነ ብርሃን፤ ኢትዮጵያ ከቀይ ባህር እንድትርቅ የተደረገበት ሴራ ስንቆጭበት የኖርንበት ጉዳይ ነው ሲሉ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ የወደቦች ባለቤት እንደነበረችና ገቢና ወጪ ምርቶችን በቀላሉ ታንቀሳቅስ እንደነበር በማስታወስ ለምን እንዳጣነው እስካሁንም ግልጽ አይደለም ብለዋል።
የባህር በር ባለቤትና የባህር ሃይል የነበራት ኢትዮጵያ ለምን እንዳጣች ማንም የማያውቀውና ጉዳዩ እንዳይነሳ ተጽእኖ ይደረግ እንደነበር አስታውሰው አሁን ላይ ግን የትውልድ ጥያቄ ሆኖ በመምጣቱ ኮርተናል ብለዋል።
በመሆኑም ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን በመገንባት ታሪክ የሰራው ትውልድ የባህር በር ባለቤትነትን ማሳካቱ የማይቀር መሆኑን እርግጠኛ ነኝ ሲሉም ተናግረዋል።
ሌላኛው የቀድሞ ሰራዊት አባል መቶ አለቃ አበባው ገብረእግዚአብሔር፤ የኢትዮጵያ የባህር በር ማጣት በብዙ መልኩ እስካሁንም የተሻገረ ችግር የፈጠረባት መሆኑን አንስተዋል።
በመሆኑም የሀገር ህልውና ጉዳይ እና የትውልዱ ጥያቄ ሆኖ መነሳቱና የባህር በር ባለቤትነት የግድ መሆኑ የሁላችንም ጽኑ አቋም ነው ሲሉ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያን ከአባይና ከቀይ ባህር ነጥሎ ማየት የማይታሰብ መሆኑን የገለጹት መቶ አለቃ አበባው፤ የባህር በር ባለቤትነታችን የማይቀር በመሆኑ ለዚህም በትብብርና በአብሮነት ለሀገራችን መስራታችን ይቀጥላል ብለዋል።