ቀጥታ፡

የኢትዮ ኮደርስ ስልጠና ሥራን በእውቀትና በቴክኖሎጂ ታግዞ ለማከናወን አስችሎናል-ሰልጣኞች

ቦንጋ፣ ነሐሴ 29/2018 (ኢዜአ)፡-የኢትዮ ኮደርስ ስልጠና ሥራቸውን በእውቀት እና በቴክኖሎጂ ታግዘው ለማከናወን እንዳገዛቸው በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል የመንግስት ሠራተኞች ገለፁ።

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ኢንሼቲቪ የሆነው የ5 ሚሊዮን ኮደርስ ስልጠና ፕሮግራም የሀገሪቱን የዲጂታል ኢኮኖሚ ሽግግር በማፋጠን ረገድ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያበረከተ ይገኛል።

በፕሮግራሙም በዋናነት በሶፍትዌር ልማት፣ በዳታ ትንተና፣ በሰው ሰራሽ አስተውሎት ክህሎት እና መሰል የቴክኖሎጂ ዘርፎች ላይ በማተኮር ለዜጎች ስልጠና እየተሰጠ ነው። 

ስልጠናውን በማስመልከት ኢዜአ ያነጋገራቸው በቦንጋ የትምህርት ኮሌጅ የፊዚክስ መምህር ሲሳይ አብደላ፣ መንግስት ባመቻቸው የኢትዮ ኮደርስ ስልጠና በአራቱም ፕሮግራሞች ሰልጥናቸውን አጠናቀው የምስክር ወረቀት መውሰዳቸውን ተናግረዋል።

ይህም ሥራቸውን በቴክኖሎጂ አስደግፈው ለማከናወን ከማገዝ ባለፈ በኦንላይን የራሳቸውን ሥራ ለመስራት ተነሳሽነት እንደፈጠረላቸው  ጠቁመዋል።


 

ሌላው የስልጠና ዕድሉ ተጠቃሚ የመንግስት ሠራተኛ ወጣት ጌጥዬ አለሙ በበኩሉ በነጻ በተሰጠው የኢትዮ ኮደርስ ስልጠና መሠረታዊ የዲጂታል እውቀቱን ማሳደጉ በስራው ተወዳዳሪ ለመሆን እንዳስቻለው ተናግሯል። 

በሶፍት ዌር ልማት፣ በዳታ ትንተና፣ በሞባይል አፕሊኬሽን ግንባታ እና በሰው ሰራሽ አስተውሎት ሰልጥኖ ምስክር ወረቀት ማግኘቱ  ሥራውን በተሻለ ጥራት ለማከናወን አስችሎታል። 

የኢትዮ ኮደርስ ስልጠና ዜጎች በተለይ ወጣቶች ከቴክኖሎጂ ጋር እንዲተዋወቁና ክህሎታቸውን እንዲያዳብሩ ትልቅ እገዛ እያደረገ ነው ያሉት ደግሞ በቦንጋ ዩኒቨርሲቲ የሒሳብ መምህር ሙሉጌታ አንዷለም ናቸው።


 

በተለይ መምህራን ሥራቸውን ወቅቱ በደረሰበት የቴክኖሎጂ አውቀት ታግዘው እንዲያከናውኑ ያግዛቸዋል ብለዋል። 

በቀጣይ በዳታ ሳይንስ እና በአርቴፌሻል ኢንተለጀንስ ላይ ስፔሻላይዝ ለማድረግ ፍላጎት እንዳደረባቸውም ጠቁሟል ።

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ኢንዱስትሪና ኢኖቬሽን ቢሮ ምክትል ሀላፊና የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ልማት ዘርፍ ሀላፊ አቶ ምትኩ አሰፋው ኢንሼቲቩ ዲጅታል ኢትዮጵያ 2030ን ለማፋጠን ትልቅ አቅም የሚፈጥር መሆኑን ገልጸዋል።


 

እንደሀገር የተጀመረው የ5 ሚሊዮን ኮደርስ ኢንሼቲቪ በቴክኖሎጂ የበቃ ተወዳዳሪ ዜጋ መፍጠርን ታሳቢ ያደረገ መሆኑን ገልጸው፣ ስልጠናውን ለመውሰድ በክልሉ ከተመዘገቡት ውስጥ እስካሁን ድረስ ከ48 ሺህ በላይ የሚሆኑት ስልጠናውን አጠናቀው የምስክር ወረቀት ወስደዋል ብለዋል።

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም