ቀጥታ፡

በደብረ ብርሃን ከተማ ሰላምን አፅንቶ በማዝለቅ የልማት ስራው እንዲፋጠን የድርሻችንን እንወጣለን-ነጋዴዎች

ደብረ ብርሃን፤ ነሐሴ 29/2018 (ኢዜአ)፡- በደብረ ብርሃን ከተማ የተገኘውን ሰላም በዘላቂነት አጠናክሮ በማስቀጠል የተጀመሩ የልማት ተግባራት ተጠናከረው እንዲቀጥሉ የድርሻቸውን እንደሚወጡ የንግዱ ማህበረሰብ አባላት ገለጹ።

የአስተዳደሩ ሰላምና ፀጥታ መምሪያ በወቅታዊ የሰላምና የመልካም አስተዳደር ሥራዎች ላይ በከተማዋ ከሚገኙ አገልግሎት ሰጪ ተቋማትና ከንግዱ ማህበረሰብ አባላት ጋር ዛሬ ውይይት አካሂዷል።

ከውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል አቶ ተስፋዬ እሸቴ እንደገለጹት፤ በከተማዋ እየተረጋገጠ የመጣውን ሰላም አፅንቶ ለማዝለቅ የሁሉንም ህብረተሰብ ርብርብ ይጠይቃል። 

በከተማዋ አሁን የተገኝው ሰላም ዘላቂ እንዲሆንና የልማት ጥያቄዎቻቸው ፈጣን ምላሽ እንዲያገኙ የድርሻቸውን እንደሚወጡም አረጋግጠዋል።

ሌላዋ የመድረኩ ተሳታፊ ወይዘሮ ሰርካለም ተሾመ፤ የከተማዋን ሰላም በዘላቂነት ለማረጋገጥና ወንጀልን በጋራ ለመከላከል ከሚመለከተው አካል ጋር በቁርጠኝነት እየሰሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።

 በተለይም አጥፊዎችን ተከታትሎ ለህግ አስከባሪ አካላት አጋልጦ በመስጠት ወንጀልን በጋራ ለመከላከል የተጀመረውን ስራ ከማገዝ አንፃር የበኩላቸውን እንደሚወጡ አስታውቀዋል።

በህብረተሰብ ተሳትፎ የብሎክ አደረጃጀትን መሰረት አድርጎ ወንጀልን አስቀድሞ ለመከላከል በተጀመረው አሰራር ውስጥ ተሳታፊ መሆናቸውን የገለጹት ደግሞ ሌላው የመድረኩ ተሳታፊ አቶ አውላቸው ለገሰ ናቸው።


 

የደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር ሰላምና ፀጥታ መምሪያ ኃላፊ አቶ ዳንኤል እሸቴ በበኩላቸው፤ የከተማዋን ሰላምና ልማት በዘላቂነት ለማረጋገጥ የንግዱ ማህበረሰብ ሚና የጎላ መሆኑን ገልጸዋል። 

ህዝቡ የሚያነሳውን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄ በተገቢው መንገድ ለመመለስ በከተማዋ የመሰረተ ልማት፣ የኢንዱስትሪና የኢንቨስትመንት ስራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥና ልማቱን ለማፋጠን የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት እና የንግዱ ማህበረሰብ አባላት የፀጥታ ኃይሉ  ወንጀልን ለመከላከል የሚያደርገውን ጥረት በማገዝ የድርሻቸውን መወጣት ይጠበቅባቸዋል ነው ያሉት።

የከተማዋን ሰላምና ደህንነት በዘላቂነት ለማረጋገጥ ማህበረሰቡና የፀጥታ ሀይሉ ተቀናጅተው ወንጀልን እየተከላከሉ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የአስተዳደሩ ፖሊስ መምሪያ አዛዥ ኮማንደር ገብረመስቀል ቦጋለ ናቸው።

ከዚህ ውስጥም  የንግዱ ማህበረሰብ በሆቴሎች አልጋ የሚይዙ እንግዶችን በአግባቡ በመመዝገብ ለፀጥታ ኃይሉ በማሳወቅ የጀመረውን ቅንጅታዊ አሰራር አጠናክሮ እንዲቀጥል አሳስበዋል።

በተካሄደው የውይይት መድረክ ከከተማዋ የተውጣጡ የአገልግሎት ሰጪና የንግዱ ማህበረሰብ አካላት ተሳትፈዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም