ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ የውሃ ሃብቶቿን ለኢነርጂ ልማት የማዋሉን ጉዞ አጠናክራ ትቀጥላለች - ኢንጂነር አሸብር ባልቻ

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 29/2018 (ኢዜአ)፡- ኢትዮጵያ የውሃ ሃብቶቿን ለኢነርጂ ልማት የማዋሉን ጉዞ አጠናክራ እንደምትቀጥል የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኢንጂነር አሸብር ባልቻ አስታወቁ።

ግብፅ ድንበር ተሻጋሪ የውሃ ሃብት ትብብርና ፍትሐዊ ተጠቃሚነት መርህን ባለመቀበል በቅኝ ግዛት ዘመን የነበረውን የአባይን ወንዝን በብቸኝነት የመጠቀም ስሁት ትርክት ለመመለስ በራሷ ዓለም እየዳከረች እንደሚገኝ አንስተዋል።

ኢንጂነር አሸብር ባልቻ ለኢዜአ እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሃብቶቿን በማልማት ሙሉ በሙሉ የመጠቀም መብት ያላት ሉዓላዊት ሀገር መሆኗን በሕዳሴ ግድብ በተግባር አስመስክራለች።

ኢትዮጵያውያን ላለፉት አሥራ አራት ዓመታት ሕዳሴውን ለማደናቀፍ የተሸረቡ ሴራዎችን በመበጣጠስ በራሳቸው አቅም ገንብተው የዓባይ ትሩፋት ተቋዳሽ የሆኑበትን ዕድል እንደፈጠሩ ገልጸዋል።

"ውሾች ይጮሃሉ ግመሏ ጉዞዋን ትቀጥላለች" እንዲሉም፤ ኢትዮጵያ ሕዳሴን እንዳሳካች ሁሉ የማንም ጩኸት ሳይገድባት እንደ ሕዳሴ ግድብ ሁሉ የውሃ ሃብቶቿን ለኢነርጂ ለማዋል ቁርጠኛ መሆኗን አረጋግጠዋል።

የታላቁ ሕዳሴ ግድብ የኢትዮጵያን የማድረግ አቅም ለዓለም የገለጠ በሕብረ-ብሔራዊ አንድነት የተገነባ ሁነኛ የትዕምርት ፕሮጀክት መሆኑንም አንስተዋል።

ሕዳሴ ግድብ መገንባቱ በታችኞቹ የተፋሰስ ሀገራት ላይ ምንም ዓይነት ጫና ሳይፈጥር ዓመቱን ሙሉ አስተማማኝ ውሃ የሚያገኙበትን ዕድል እንደፈጠረ አብራርተዋል።

ግብፅም አስተማማኝ የውሃ ፍሰት እያገኘችና ግድቦቿም ሙሉ ሆነው ሳለ የምታስተጋባው ጩኸት ፍጹም ሐሰት መሆኑን አስታውቀዋል።

ኢትዮጵያ በመደመር እሳቤ አብሮ የማደግ ቀጣናዊ የኢኮኖሚ ትስስርና ትብብር መርህ በውሃ ሃብቶቿ ላይ የምታመነጨውን ኃይል ለጎረቤቶቿ በማቋደስ ተጠቃሚ እያደረገች መሆኗን ተናግረዋል።

በዚህም ኢትዮጵያ ማንም ስለጮኸ ሃብቶቿን አልምታ ከመጠቀም የሚያግዳት አካል የለም ያሉት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፤ ግብጽ የምታሰራጨው የተዛባ መረጃም የተፈጥሮ ሃብቶቻችንን በማልማት ዕድገትና ብልፅግናን እንዳናረጋግጥ የማድረግ ሴራ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ የልማት አቅጣጫ ሌሎችን በመጉዳት ላይ የተመሠረተ አይደለም ያሉት ኢንጂነር አሸብር፤ በልማት ትሩፋቶች አብሮ በማደግ መርህ ለሌሎች በማቋደስ እየተንቀሳቀሰች ነው ብለዋል።

አሁንም ወደፊትም ትልቁ የኃይል ምንጫችን ወንዞቻችን ናቸው ያሉት ኢንጂነር አሸብር፤ ወንዞቻችንን ወደ ልማት ለመቀየር ጥናትን መሰረት በማድረግ እየተሰራ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም