ቀጥታ፡

በብሄረሰብ አስተዳደሩ የወባ በሽታ ወረርሽኝን ለመከላከል የፀረ ወባ ኬሚካል ርጭት እየተካሄደ ነው

ሰቆጣ፤ ነሃሴ 29/2018(ኢዜአ)፡- በአማራ ክልል በዋግ ኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር የወባ በሽታ ወረርሽኝን ለመከላከል የሚያስችል የፀረ ወባ ኬሚካል ርጭት እየተካሄደ እንደሚገኝ የአስተዳደሩ ጤና መምሪያ  ገለፀ።

በመምሪያው የወባና ሌሎች በሽታዎች መከላከልና መቆጣጠር ባለሞያ አቶ አበበ በለጠ ለኢዜአ እንዳሉት  በብሄረሰብ አስተዳደሩ  የወባ  በሽታን ለመከላከል የተጠናከረ ስራ እየተከናወነ ነው።

በተያዘው በጀት ዓመትም 125 ሺህ በላይ የመኝታ አጎበር  ለህብረተሰቡ ከመሰራጨቱ በተጨማሪ በ38 ሺህ  መኖሪያ ቤቶች ላይም ፀረ ወባ የኬሚካል ርጭት  እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።

የኬሚካል ርጭቱ  የወባ በሽታ ወረርሽኝ  በከፍተኛ ሁኔታ በሚስተዋልባቸው  በሰሃላ፣ ሰየምትና አበርገሌ ወረዳዎች መሆኑን አስረድተዋል።

ከከሚካል ርጭት በተጨማሪ  ለትንኝ መራቢያ ምቹ የሆኑ  ያቆረ ውሀን  የማፋሰስ፣ የማደፈንና አካባቢውን  ንፁህ የማድረግ  ስራ  የበሽታውን  ስርጭት ለመቀነስ እንዲቻል ህብረተሰቡን ያሳተፉ ተግባራት መከናወናቸውን አብራርተዋል።

በሰሃላ ወረዳ የመሸሀ ከተማ ነዋሪ  ወይዘሮ የሺዓለም ሙላቴ እንዳሉት በክረምቱ በአካባቢያቸው ባጋጠመ የዝናብ መቆራረጥ የወባ ትንኝ እንዲራባ ምቹ ሁኔታ በመፈጠሩ  ስጋት አድሮባቸው እንደነበር ገልፀዋል።

አሁን ላይ በሚኖሩበት ቀበሌ የተካሄደው የቤት ለቤት የፀረ ትንኝ ኬሚካል ርጭት ስጋታቸውን በማስወገድ እፎይታ  እንደፈጠረላቸው  ተናግረዋል።

ወባን ለመከላከል ለመራቢያ ምቹ  የሆኑና ውሃ  ያቆሩ ቦታዎችን የማጽዳት፣ የማፋሰስና የማዳፈን ስራ እየተከናወነ መሆኑን የገለጹት ደግሞ ወይዘሮ አለም ፀሃይ ሽሙ ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም