ቀጥታ፡

የኢትዮ ኮደርስ ስልጠና የዲጂታል ክህሎታችንን በማሳደግ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ አድርጎናል- ወጣቶች

ጎንደር፤ ነሐሴ 29/2018 (ኢዜአ)፡-የኢትዮ ኮደርስ ስልጠና የዲጂታል ክህሎታችንን በማሳደግ ለስራ እድል ፈጠራ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ለመሆን ከፍተኛ እገዛ እያደረገልን ነው ሲሉ ሰልጣኞች ገለጹ።

በዚሁ ጉዳይ ላይ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የጎንደር ከተማ ወጣቶች እንዳሉት፣ የኢትዮ ኮደርስ ስልጠና ዘመኑ የሚጠይቀውን የዲጂታል ቴክኖሎጂ ክህሎታቸውን እና ተወዳዳሪነታቸውን አሳድጓል።

አስተያየታቸውን ከሰጡ ወጣቶች መካከል በውሃ ምሕንድስና ሁለተኛ ዲግሪውን ያጠናቀቀው ዮሐንስ መልኬ ፤ የኢትዮ ኮደርስ ስልጠና የመረጃ ትንተና እና የሰው ሰራሽ አስተውሎት ክህሎቴን ለማሳደግ አስችሎኛል ነው የሚለው።

በትምህርት ወቅት የምርምር ስራ በሚያካሒድበት ወቅት መረጃዎችን በቀላሉ ለማደራጀት የተሻለ ክሕሎት እንዲኖረው በማድረጉ በአራት ነጥብ ውጤት ለመመረቅ እንደረዳውም ነው የተናገረው።

በተሰማራበት የስራ መስክም ዓለም አቀፍ የቴክኖሎጂ አሰራሮችን፣ የጤና አጠባበቅ እና የምግብ ስርዓትን በቀላሉ በመገንዘብ ምርታማነትን ለማሳደግ ስልጠናው የላቀ ሚና እንዳበረከተለት ነው ያረጋገጠው።


 

ወጣት ፍሬው ይግዛው በበኩሉ ከስልጠናው የሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI)፣ የፕሮግራሚንግ እና የመሰረታዊ ዳታ ሳይንስ እውቀትን  በማግኘት በዲጂታል ቢዝነስ ዘርፍ ለመሰማራት እንደቻለ ነው የጠቀሰው። 

የኮደርስ ስልጠና በቴክኖሎጂው ዓለም አዳዲስ ግኝቶችን በቀላሉ ለመረዳት እና ከዓለም አቀፍ አሰራሮች ጋር አብሮ ለመራመድ የሚያስችሉ ዘመናዊ እሳቤዎችን ለመገንባት ትልቅ አቅም እንደፈጠረለትም ተናግሯል።


 

የጎንደር ከተማ አስተዳደር ስራ እና ክህሎት መምሪያ ተወካይ ኃላፊ አቶ አካሌ ፀጋይ እንደገለጹት፣ የኮደርስ ስልጠና በቴክኖሎጂ ዘርፍ እና በስራ እድል ፈጠራ የወጣቶችን ተጠቃሚነት እያሳደገ ይገኛል።

የመንግስት ሰራተኞችን እና ወጣቶችን በስልጠናው በማሳተፍ የዲጂታል ክህሎታቸውን በማዳበር በሀገር ውስጥ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ በመሆን ተጨማሪ የስራ እድል እንዲያገኙ ለማድረግ እየተሰራ ነው ብለዋል።

በተጠናቀቀው በጀት ዓመትም ስልጠናቸውን ላጠናቀቁ 44 ሺህ 962 ዜጎች የምስክር ወረቀት ማግኘታቸውን ነው ያመለከቱት። 

በቀጣይም በከተማው የሚገኙ የመንግስት እና የግል ኮሌጆች የኮምፒውተር ክፍሎችን እና አሰልጣኝ መምህራንን በመጠቀም ስልጠናውን በስፋት ለማከናወን እንደሚሰራ አስረድተዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም