ቀጥታ፡

በካፍ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ  ከአል ሂላል ጋር ይጫወታል

 አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 29/2018 (ኢዜአ):-  በካፍ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ የመጀመሪያ ቅድመ ማጣሪያ ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ከሱዳኑ አል ሂላል ጋር የመጀመሪያ ጨዋታውን ዛሬ ያደርጋል።

 ጨዋታው ምሽት ሁለት ሰዓት ላይ በሩዋንዳ በሚገኘው ኪጋሊ ፔሌ ስታዲየም ይካሄዳል።
 
ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ በአህጉራዊው መድረክ ለመሳተፍ የበቃው በኢትዮጵያ ዋንጫ ፍጻሜ ሲዳማ ቡናን 2 ለ 0 አሸንፎ ሻምፒዮን መሆኑን ተከትሎ ነው።
 
ወልዋሎ በካፍ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ሲሳተፍ በክለቡ የ70 ዓመታት ታሪክ የአሁኑ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።
 
በአሰልጣኝ ግርማ ታደሰ የሚመራው ወልዋሎ ለቅድመ ማጣሪያው ጨዋታው ዝግጅቱን ሲያደርግ ቆይቷል።
 
ካርሎስ ዳምጠው፣ በረከት ሳሙኤል፣ እዮብ አለማየሁ እና አህመድ ረሺድን ጨምሮ የተለያዩ ተጫዋቾችን በክረምቱ የተጫዋቾች የዝውውር መስኮት መስኮት በማስፈረም ስብስቡን አጠናክሯል።
 
ክለቡ ካስፈረማቸው ተጫዋቾች ባሻገር የጌቱ ኃይለማርያም እና አፈወርቅ ኃይሉን ጨምሮ የሌሎች ተጫዋቾችን ውል አራዝሟል።
 
ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ በ2018 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ በ46 ነጥብ 16ኛ ደረጃን ይዞ ማጠናቀቁ ይታወሳል።
 
ተጋጣሚው አል ሂላል በካፍ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ሲሳተፍ የአሁኑ ለሁለተኛ ጊዜ ነው።
 
የሱዳኑ ክለብ ለመጨረሻ ጊዜ በውድድሩ ላይ የተሳተፈው እ.አ.አ በ2022/23 የውድድር ዓመት እንደነበር መረጃዎች ያመለክታሉ።
 
በአሰልጣኝ ናዲር ዛርግ አክላንድ  የሚመራው አል ሂላል በአህጉራዊ ውድድሮች ላይ የረጅም ጊዜ የተሳትፎ ልምድ አለው።
 
እ.አ.አ በ1937 የተመሰረተው አል ሂላል አንጋፋ የሚባል ክለብ ነው።
 
የሁለቱ ክለቦች የመልስ ጨዋታ መስከረም 2 ቀን 2019 ዓ.ም በድሬዳዋ ስታዲየም ይካሄዳል።
 
ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ በደርሶ መልስ ውጤት ካሸነፈ በሁለተኛ ዙር ከዛንዚባሩ ኬኤምኬኤም  እና ከሊቢያው አል አህሊ ትሪፖሊ አሸናፊ ጋር የሚጫወት ይሆናል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም