ቀጥታ፡

የሰው ሰራሽ አስተውሎት አጠቃቀምን ከአባል ሀገራት ብሔራዊ የሕግ ማዕቀፎች ጋር የተጣጣመ ቀጣናዊ የጋራ ቁጥጥር ሥርዓት መዘርጋት ያስፈልጋል-ወርቅነህ ገበየሁ(ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 29/2018 (ኢዜአ)፦ የሰው ሰራሽ አስተውሎት አጠቃቀምንና የመረጃ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ከአባል ሀገራት ብሔራዊ የሕግ ማዕቀፎች ጋር የተጣጣመ ቀጣናዊ የጋራ ቁጥጥር ሥርዓት መዘርጋት እንደሚያስፈልግ የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ-መንግሥታት ባለሥልጣን (ኢጋድ) ዋና ፀሐፊ ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር) ገለጹ።

ከዛሬ ነሐሴ 29 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ ለሁለት ቀናት የሚቆየውና የኢጋድ አባል ሀገራት ተወካዮችና ባለድርሻ አካላት የተሳተፉበት፣ የቀጣናውን የሰው ሰራሽ አስተውሎት ስትራቴጂ በጋራ ለመቅረጽ ያለመ አውደ ጥናት መካሄድ ጀምሯል።


 

የኢጋድ ዋና ፀሐፊ ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ የሰው ሰራሽ አስተውሎት ፈጣን ዕድገት የዓለም ኢኮኖሚን፣ መንግሥታትንና የሰውን አቅም እየቀረጸ ይገኛል።

ሰው ሰራሽ አስተውሎት እና የዲጂታል ዘርፍ የቀጣናዊ ኢኮኖሚ ውህደትን በማፋጠን ለማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ወሳኝ ኃይል መሆኑንም ገልጸዋል።

የምሥራቅ አፍሪካ ልማት በይነ-መንግሥታት ባለሥልጣን (ኢጋድ) አባል ሀገራትም የሰው ሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂ አማራጭን በአግባቡ በመጠቀም የኢኮኖሚ ውህደትን ማፋጠን እንዳለባቸው ተናግረዋል።

ለዚህም የሰው ሰራሽ አስተውሎት አጠቃቀም እና የመረጃ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ፣ ከአባል ሀገራት ብሔራዊ የሕግ ማዕቀፎች ጋር የተጣጣመ ቀጣናዊ የጋራ ቁጥጥር ሥርዓት መዘርጋት እንደሚገባ አሳስበዋል።

በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የኢጋድ ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ከተማ ኃይሌ በበኩላቸው፤ ሰው ሰራሽ አስተውሎት የኢኮኖሚ ዕድገትን የሚያፋጥንና ብዝኅ ምርታማነት አቅም መገንቢያ እየሆነ መምጣቱን ገልጸዋል።

በዚህም ሰው ሰራሽ አስተውሎትን ለቀጣናዊ ትብብር፣ ለጠንካራ የፖሊሲ ማዕቀፍ ዝግጅት፣ ለዲጂታል መሠረተ ልማት፣ እንዲሁም ለጥናትና ፈጠራ ኢንቨስትመንት መጠቀም እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።

ኢትዮጵያ በሀገራዊ እና ቀጠናዊ ልማት ውስጥ የዲጂታል ቴክኖሎጂዎችንና የሰው ሰራሽ አስተውሎትን ሚና በመገንዘብ ከኢጋድ አባል ሀገራት ጋር በትብብር ለመሥራት ቁርጠኛ መሆኗንም ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ እየተገነባ ያለው የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ዩኒቨርሲቲም የኢጋድ አባል ሀገራትን እና አጠቃላይ አፍሪካን የሚጠቅም እንደሚሆን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም