በሀረሪ ክልል የክረምት በጎ ፍቃድ አገልግሎት የመደጋገፍ እሴት በማጎልበት የዜጎችን ህይወት በላቀ ደረጃ እየቀየረ ይገኛል - አቶ ጌቱ ዋዬሳ - ኢዜአ አማርኛ
በሀረሪ ክልል የክረምት በጎ ፍቃድ አገልግሎት የመደጋገፍ እሴት በማጎልበት የዜጎችን ህይወት በላቀ ደረጃ እየቀየረ ይገኛል - አቶ ጌቱ ዋዬሳ
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 29/2018 (ኢዜአ):- በሐረሪ ክልል በክረምት በጎ ፍቃድ አገልግሎት የመደጋገፍ እሴትን በማጎልበት የዜጎችን ህይወት በላቀ ደረጃ እየቀየረ ይገኛል ሲሉ በብልጽግና ፓርቲ የሀረሪ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ጌቱ ዋዬሳ ገለጹ።
በሀረሪ ክልል በክረምት በጎ ፍቃድ እየተከናወኑ በሚገኙ ተግባራት ዙሪያ ውይይት ተደርጓል።
በመድረኩ ላይ የተገኙት በብልፅግና ፓርቲ የሀረሪ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጌቱ ወዬሳ እንደገለፁት ፣ በክልሉ በክረምት በጎ ፍቃድ አገልግሎት የአብሮነትና መደጋገፍ እሴትን በማጎልበት የዜጎችን ህይወት በላቀ ደረጃ እየቀየረ ይገኛል።
የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በተደመረ አቅም ዜጎችን በማገዝና ሃብትን አቀናጅቶ በመምራት ረገድ የላቀ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል ብለዋል።
በተለይም በክረምቱ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በርካታ አቅመ ደካሞችንና አረጋውያንን ተጠቃሚ ያደረጉ በርካታ ስራዎች እውን ማድረግ መቻሉን አንስተዋል።
በዘንድሮ የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎትም የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት የሚያጎለብቱ 14 ተግባራት በተጠናከረ መልኩ እየተከናወኑ እንደሚገኙ ነው የተናገሩት።
በአሁኑ ወቅት የአረጋውያንና አቅመ ደካሞች መኖሪያ ቤት እድሳትና መልሶ ግንባታ፣ የአካባቢ ንጽህና ጥበቃ፣ ችግኝ ተከላ፣ ደም ልገሳ፣ የማጠናከሪያ ትምህርት የመስጠትና ሌሎች ተግባራት በመከናወን ላይ እንደሆኑም አንስተዋል።
ከዚህ በተጨማሪም ማዕድ ማጋራት፣ አዳዲስና ነባር የመማሪያ ክፍል ግንባታ እና እድሳት ፣ የትምህርት ቤቶች የተማሪ ወንበሮች ጥገና፣ ጽዳትና ውበት ስራዎችን ጨምሮ የማጣቃሻ መጽሀፍት የማሰባሰብ ስራ በበጎ ፍቃድ አገልግሎቱ የትኩረት የተሰጣቸው ጉዳዮች መሆናቸውን ገልጸዋል።
የበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ መደጋገፍ፣ የመተጋገዝና አብሮነትን ይበልጥ የሚያጠናክር መሆኑን ጠቁመው የዜጎችን እውቀት፣ ገንዘብ፣ ጉልበት እና ሌሎች ምቹ ሁኔታዎችን በሚገባ መጠቀምና ከድህነት መላቀቅ እንደሚያስፈልግ ነው የጠቆሙት።
ይህ የመተጋገዝና የአብሮነት ባህል ድህነትን ለማሸነፍ ትልቅ አቅም የሚፈጥር በመሆኑ፣ አመራሩ የታቀዱትን ግቦች ወደ ሙሉ ተግባር ለመቀየር እያከናወነ የሚገኘውን ተግባራት ማጠናከር እንዳለበት አቶ ጌቱ አሳስበዋል።
እንዲሁም በክልሉ አምስቱ የጳጉሜ ቀናት የሚከናወኑ መርሃ-ግብሮች የተሳኩ እንዲሆኑ ሁሉም የመንግስት ተቋማት፣ በየደረጃ የሚገኝ አመራር፣ የመንግስት ሠራተኞችና መላው ሕዝቡ የሚጠበቅበትን ድርሻ እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል፡፡