ቀጥታ፡

መተግበሪያው የኢትዮጵያ 2030 የዲጂታል ጉዞ ግቦች ዕውን እንዲሆኑ የራሱን አስተዋጽኦ ያበረክታል- ኢንጂነር ታከለ ኡማ

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 29/2018 (ኢዜአ)፡-የዲጂታል መተግበሪያው መጀመር የኢትዮጵያ 2030 የዲጂታል ጉዞ ግቦች ዕውን እንዲሆኑ የራሱን አስተዋጽኦ የሚያበረክትበት ምዕራፍ መሆኑን የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ቦርድ አባል እና የኢትዮ-ጂቡቲ ባቡር ትራንስፖርት አክሲዮን ማህበር ዋና ስራ አስፈጻሚ ኢንጂነር ታከለ ኡማ ገለጹ።

የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ደንበኞች በዘመናዊ ዲጂታል አማራጭ የሚገለገሉበት የዲጂታል መተግበሪያ ዛሬ አስመረቋል።


 

የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ የቦርድ አባልና የኢትዮ-ጂቡቲ ባቡር ትራንስፖርት አክሲዮን ማህበር ዋና ስራ አስፈጻሚ ታከለ ኡማ (ኢ/ር) ፤ ዛሬ የሚጀምረው ቴክኖሎጂ ትልቅ ትርጉም ያለውና ደንበኞች የተሻለ እንዲሁም ውጤታማ አገልግሎት እንዲያገኙ የሚያስችል መሆኑን አመልክተዋል። 

መንግስት የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ የምስራቅ አፍሪካ ትልቅ ተቋም እንዲሆን እንደሚፈልግ አንስተዋል።

ይህንንም ለማስቻል በርካታ ውጤታማ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።

ይፋ የተደረገው የዲጂታል አገልግሎት የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ጉዞን ለማሳካት የተያዙ ግቦች ዕውን እንዲሆኑ የራሱን ሚና የሚወጣበት ምዕራፍ መሆኑን ገልጸዋል።


 

የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ዋና ስራ አስፈጻሚ አብዱልበር ሸምሱ (ኢ/ር) በበኩላቸው፤ ድርጅቱ እያደገ ያለውን ኢኮኖሚ  የሚመጥን አገልግሎት ለመስጠት አሰራሩን እያዘመነ ይገኛል።

አገልግሎት አሰጣጡን ፈጣን፣ ቀልጣፋና ተደራሽነት ለማረጋገጥ በዲጂታል ቴክኖሎጂ ላይ ትኩረት ማድረጉን አስታውቀዋል።

ዛሬ የተመረቀው የዲጂታል መተግበሪያ የአገልግሎት አሰጣጡን የበለጠ በማዘመን ለደንበኞች ቀልጣፋ አገልግሎት መስጠት እንደሚያስችል ገልጸዋል።

ደንበኞች በመተግበሪያው አማካኝነት በሞባይል ስልካቸው እንዲመዘገቡ፣ የሂደት ክትትል እንዲያደርጉ እና ተያያዥ አገልግሎቶችን በፍጥነትና በምቾት እንዲያገኙ ያስችላል ብለዋል።

በቀጣይም በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ለማድረግና ውጤታማ አገልግሎት ለመስጠት የዲጂታል ቴክኖሎጂ የማጠናከር ተግባር እንደሚቀጥል ገልጸዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም