ቀጥታ፡

ለመጪው አዲስ ዓመት የግብርናና ኢንዱስትሪ ምርቶችን ለማቅረብ በቂ ዝግጅት ተደርጓል

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 29/2018 (ኢዜአ)፡-ለመጪው አዲስ ዓመት የግብርናና ኢንዱስትሪ ምርቶችን በስፋት ለማቅረብ በቂ ዝግጅት መደረጉን የአዲስ አበባ ኅብረት ሥራ ኮሚሽን ገለጸ።

ኮሚሽኑ የ2019 ዓ.ም የዘመን መለወጫ በዓልን በማስመልከት ለበዓሉ አስፈላጊ የሆኑ የግብርናና ኢንዱስትሪ ምርቶችን የአቅርቦት ዝግጅት በተመለከተ መግለጫ ሰጥቷል።

ኮሚሽነር ሽታዬ መሐመድ እንደገለጹት፤ ህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማጎልበት የሸማቾች ኅብረት ሥራ ማህበራት የሪፎርም ሥራዎች ተከናውነዋል።

ከመጪው በዓላት ጋር ተያይዞ አስፈላጊ ግብዓቶችን ለህብረተሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ ለማቅረብ የሚያስችሉ የዋጋ ጥናቶችን በማድረግ የትስስር ሥራዎች ተሰርተዋል ብለዋል።

በዚህም ለአዲስ ዓመት፣ የመስቀልና የኢሬቻ በዓላት ምርቶች በተመጣጣኝ ዋጋ ለህብረተሰቡ ለማቅረብ ከፌዴራል ኅብረት ሥራ ኮሚሽንና ከክልሎች ማህበራት ጋር የአቅርቦት ትስስር መፈጠሩን ገልጸዋል።

የጤፍ፣ የዱቄትና ሌሎች የግብርናና የኢንዱስትሪ ምርቶች ለህብረተሰቡ ተደራሽ እንዲሆኑ ከአምራች ኢንዱስትሪዎችና ዩኒየኖች ጋር ትስስር መፈጠሩን ለአብነት ጠቅሰዋል።

የእንቁላልና የዶሮ ምርቶች፣ የሽንኩርት እንዲሁም የዘይት አቅርቦትም ተደራሽ ለማድረግ ከአምራቾችና ከአስመጪዎች ጋር ትስስር መፈጠሩን አክለዋል።

የስጋ አቅርቦትን በተመለከተም የሸማች ማህበራት ለህብረተሰቡ እንዲያቀርቡና የገበያ አማራጮችን የማስፋት ሥራዎች መከናወኑን ገልጸዋል።

የገበያ አማራጮችን ለማስፋት ከባለድርሻ አካላት ጋር በጋራ በመሆን ለህብረተሰቡ በዩኒየን፣ በቅዳሜና እሁድ ገበያዎችና በባዛሮች ምርቶች በስፋት መቅረባቸውንም አንስተዋል።

በሁሉም ክፍለ ከተሞች ኤግዚቢሽንና ባዛር መዘጋጀታቸውንና ከ700 በላይ በሸማች ሱቆች፣ በ154 በመሰረታዊ ሸማች ማህበራት ምርቶች መቅረባቸውን ገልጸዋል።

ከባለድርሻ አካላት ጋር የሚከናወኑ የገበያዎችን ተደራሽነት የማስፋትና የማዘመን ሥራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም