በጉራጌ ዞን ተፈጥሮዊ እና ባህላዊ እሴቶች ለምተው ለቱሪስት መስህብ እየዋሉ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በጉራጌ ዞን ተፈጥሮዊ እና ባህላዊ እሴቶች ለምተው ለቱሪስት መስህብ እየዋሉ ነው
ወልቂጤ፣ነሐሴ 29/2018 (ኢዜአ)፡-በጉራጌ ዞን ተፈጥሯዊ እና ባህላዊ እሴቶች ለምተው ለቱሪስት መስህብ እየዋሉ መሆኑን የጉራጌ ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ አስታወቀ።
የጉራጌ ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ሃላፊ ወይዘሮ መሰረት አመርጋ በዞኑ ተሸፍነው የቆዩ ባህላዊ፣ ታሪካዊ እና ተፈጥሮዊ ቅርሶች በመደመር መንግስት እሳቤ ለምተው ለቱሪስት መስህብነት እየዋሉ ነው።
የቱሪስት ሀብቶችን በማልማትና በማስተዋወቅ ለሁለንተናዊ ብልጽግና ለማዋል ባለድርሻ አካላትን ባሳተፈ መልኩ እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።
ለአብነትም በዞኑ ሀይማኖታዊና ባህላዊ በዓላትን እንዲሁም መስህቦችን በማስተዋወቅና የገጠር ኮሪደርን ከጀፎረ ባህላዊ እሴት ጋር በማስተሳሰር ለቱሪዝም ልማቱ መዋል መቻሉን ጠቁመዋል።
ይህም የቱሪስቶችን ቁጥርና የቆይታ ጊዜ በማራዘም ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ ማገዙን ገልጸዋል።
በዚህም በ2018 በጀት ዓመት ዞኑ ከ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ የሃገር ውስጥ እና የውጭ ቱሪስቶች መጎብኘታቸውና ከ6 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ መገኘቱን ተናግረዋል።
በወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ የቋንቋ፣ ባህል እና ሃገር በቀል ልማት ማዕከል ዳይሬክተር ፀጋማርያም ዱላ (ዶ/ር) ዩኒቨርሲቲው ሀገር በቀል እውቀቶችንና እሴቶችን በማልማት ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ፋይዳቸውን ለማጉላት የሚደረገውን ጥረት በጥናትና ምርምር እያገዘ ነው።
ይህም ቅርሶች የሚጠበቁበት እና ተፈጥሮና ሰው ሰራሽ የቱሪስት መስህቦች በስፋት የሚጎበኙበትን አቅም እያሳደገው መጥቷል ብለዋል።
የጉራጌ ባህላዊ እሴት የሆነው ጀፎረን በገጠር ኮሪደር ይበልጥ እንዲለማ መደረጉና መተዋወቁ ቱሪስቶች በብዛት ወደ አካባቢው እንዲመጡ ማድረጉን የተናገሩት ደግሞ አቶ ወንድሙ ብሩ ናቸው።
ይህም በቱሪዝም አገልግሎት ዘርፍ ለተሰማሩ ሰዎች የገቢ ምንጭ እየሆነ መምጣቱን ተናግረዋል።