በአማራ ክልል ከ 10 ሺህ በላይ ሄክታር መሬት ላይ የዘር ብዜት ስራ እየተከናወነ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በአማራ ክልል ከ 10 ሺህ በላይ ሄክታር መሬት ላይ የዘር ብዜት ስራ እየተከናወነ ነው
ባህርዳር ፤ነሐሴ 29/2018 (ኢዜአ)፡- በአማራ ክልል የምርጥ ዘር አቅርቦት እጥረትን ለማቃለል በ10 ሺህ 456 ሄክታር መሬት ላይ የዘር ብዜት ስራ እየተከናወነ መሆኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።
የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እና የግብርና ምርታማነትን ለማሳደግ የምርጥ ዘር አቅርቦት ወሳኝ ድርሻ አለው።
በአማራ ክልል ለሚያጋጥመው የምርጥ ዘር እጥረት ዘላቂ መፍትሔ ለመስጠት እና የአካባቢውን የስነ-ምህዳር ሁኔታ ያገናዘበ ምርጥ ዘር ለአርሶ አደሩ በበቂ ሁኔታ ለማቅረብ፣ የክልሉ ግብርና ቢሮ ትኩረቱን በሀገር ውስጥ የዘር ብዜት ላይ አድርጎ እየሰራ ይገኛል።
ይህ በ10 ሺህ 456 ሄክታር መሬት ላይ የተጀመረው የዘር ብዜት ስራም የውጭ ዘር ጥገኝነትን ከመቀነስ ባለፈ፣ ለቀጣዩ ምርት ዘመን ገበሬው ጥራት ያለውና በሽታን የመቋቋም አቅሙ የጎለበተ የሰብል ዘር በቅርበትና በወቅቱ እንዲያገኝ ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረክታል።
በክልሉ ግብርና ቢሮ የሰብል ልማትና ጥበቃ ዳይሬክተር ማንደፍሮ አስላከ (ዶ/ር) ለኢዜአ እንደገለጹት የሰብል ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የተሻሻሉ የሰብል ዝርያዎችን ለአርሶ አደሩ ተደራሽ ለማድረግ የዘር ብዜት ስራ እየተከናወነ ነው።
በዚህም ከምርምር የወጡ የተሻሻሉ የሰብል ዝርያዎችን በ2018/2019 የምርት ዘመን በኩታ ገጠም እርሻ ዘር የማባዛት ስራ ትኩረት ተሰጥቶ እየተከናወነ እንደሚገኝ አስረድተዋል።
በምርት ዘመኑ በ10 ሺህ 456 ሄክታር መሬት ላይ እየተባዙ ያሉት የበቆሎ፣ የስንዴ፣ የጤፍ፣ የሩዝ፣ የአኩሪ አተርና ሌሎች የተሻሻሉ የሰብል ዘሮች እንደሆኑም አመልክተዋል።
የዘር ብዜት ስራው በአማራ ምርጥ ዘር ኢንተርፕራይዝ፣ በግል ዘር አባዥዎች፣ በዩኒየኖች፣ በኢትዮጵያ ግብርና ስራዎች ኮርፖሬሽንና ሌሎች ዘር አባዢ ድርጅቶች እየተከናወነ መሆኑንም ተናግረዋል።
በምርት ዘመኑ 267 ሺህ ኩንታል ጥራቱን የጠበቀ ምርጥ ዘር ይሰበሰባል ተብሎ እንደሚጠበቅ የገለፁት ዳይሬክተሩ፤ ይህም የክልሉን የምርጥ ዘር እጥረት በማቃለል ረገድ የጎላ ድርሻ ይኖረዋል ብለዋል።
በምዕራብ ጎጃም ዞን የሚገኘው የዕድገት ዩኒየን ስራ አስኪያጅ አቶ ተስፋዬ በሪሁን እንዳሉት ዩኔየኑ በ360 ሄክታር መሬት ላይ የስንዴ፣ የበቆሎና ባቄላ ሰብሎች የምርጥ ዘር ብዜት ስራ እያከናወነ ነው።
የዘር ብዜት ተግባሩን እያከናወነ ያለው ከ4 ሺህ 100 አርሶ አደሮች ጋር የኮንትራት እርሻ የውል ስምምነት በመፈፀም መሆኑንም ስራ አስኪያጁ ገልፀዋል።
ዩኔየኑ ባለፈው የምርት ዘመን አባዝቶ ከሰበሰበው ከሰባት ሺህ ኩንታል በላይ ምርጥ ዘር ዘንድሮ የተሻለ ይሰበስባል ተብሎ እንደሚጠበቅም ተናግረዋል።