ቀጥታ፡

በደቡብ ኦሞ ዞን የእንስሳት ጤናን በመጠበቅ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታቸውን ለማሳደግ ትኩረት ተሰጥቷል

ጂንካ፤ ነሐሴ 29/2018 (ኢዜአ)፡-በደቡብ ኦሞ ዞን የእንስሳት ዝርያን በማሻሻልና ጤንነታቸውን በመጠበቅ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታቸውን ለማሳደግ ትኩረት መሰጠቱን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ።

የደቡብ ኦሞ ዞን ግብርና መምሪያ ኃላፊ ምንላርገው አዲሱ ለኢዜአ እንዳሉት በዞኑ ካለው ከፍተኛ የእንስሳት ሀብት  የሚገኘውን የኢኮኖሚ ጥቅም ለማሳደግ የዝርያ ማሻሻልና የእንስሳቱን ጤና መጠበቅ ላይ በትኩረት እየተሰራ ነው።

በአሁኑ ወቅትም የእንስሳት ጤናን ለመጠበቅ የእንስሳት ክትባት በዞኑ ባሉ ስድስት ወረዳዎች እና ሁለት ከተማ አስተዳደሮች በዘመቻ እየተሰጠ መሆኑን ገልጸዋል።

በዘመቻ እየተሰጠ ያለው ክትባት አባሰንጋ፣ አባ ጎርባ፣ ጉርብርብ፣ የዳልጋ ከብቶች የሳንባ በሽታ፣ የዶሮ ፈንግል እንዲሁም የበግና ፍየሎች በሽታን ለመከላከል የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል።


 

በዚህም በግ፣ ፍየል፣ የዳልጋ ከብቶችና ዶሮን ጨምሮ ወደ 3 ሚሊዮን ለሚጠጉ እንስሳት በተንቀሳቃሽ የሕክምና ቡድን አማካኝነት በዘመቻ ክትባት እንደሚሰጥ ገልጸው፣ ለዘመቻው የተለያዩ ተቋማት አስተዋጾ ማድረጋቸውንም ተናግረዋል።   

በዞኑ በናፀማይ ወረዳ እንጨቴ ቀበሌ እየተሰጠ ባለው የእንስሳት ክትባት ተጠቃሚ ከሆኑ አርብቶ አደሮች መካከል ኦይታ ሞርዴ  እንዳሉት፣ መንግስት ከብቶቻቸውን በነጻ እንዲያስከትቡ ማመቻቸቱ  ጤናቸውን ለመጠበቅ አግዟቸዋል።

አቶ ባካ ዋልታ የተባሉ ሌላው የቀበሌው ነዋሪ በበኩላቸው፣ መንግስት ለከብቶቻቸው የሕክምና አገልግሎትን በአቅራቢያቸው ከመስጠት ባለፈ በዘመቻ መከተቡ ከብቶቻቸውን ከጉዳት ለመከላከል  እንደሚያስችል ተናግረዋል፡፡

በተያዘው በጀት ዓመት በዞኑ 14 ሚሊዮን የሚጠጉ ከብቶችን በመደበኛና በዘመቻ መልክ ለመከተብ መታቀዱን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታውቋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም