ለኢትዮጵያ የቤት ልማት አዲስ ምዕራፍ የከፈተ ስምምነት - ኢዜአ አማርኛ
ለኢትዮጵያ የቤት ልማት አዲስ ምዕራፍ የከፈተ ስምምነት
የኢትዮጵያ የከተሞች ዕድገት ፈጣን እየሆነ በመምጣቱ እና የሕዝብ ቁጥር ዕድገት ከዕለት ወደ ዕለት እየጨመረ በመሄዱ፣የዜጎችን የቤት ባለቤትነትን ጥያቄ በዘላቂነት መመለስ የመንግሥት አንዱ ዋና የትኩረት አቅጣጫ ሆኗል።
ባለፉት ዓመታት የነበረው የቤት አቅርቦት በመንግሥት ትከሻ ላይ ብቻ የወደቀ በመሆኑ፣ ካለው ሰፊ የሕዝብ ፍላጎት ጋር አብሮ ለመሄድ ፈታኝ ሆኖ ቆይቷል።
ይህንን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት መንግሥት አዲስ የቤት ልማት ፖሊሲ ቀርጾ በካቢኔ ማጽደቁ ይታወቃል። ፖሊሲው የዕድገቱን ፍጥነት እና የከተሞችን ነባራዊ ሁኔታ ታሳቢ ያደረገ ነው።
በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች እየተከናወኑ ያሉ የኮንስትራክሽንና የከተማ ልማት ሥራዎች ለዚህ ሰፊ ራዕይ ግልጽ ማሳያዎች ናቸው።
በዚህ ረገድ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው ባደረጉት ንግግር፤ መንግሥት ባለፉት አምስት ዓመታት ብቻ በመላ ሀገሪቱ 1.2 ሚሊዮን ቤቶችን መገንባት መቻሉን አስታውሰዋል።
ይህንኑ ስኬት መሠረት በማድረግ፣ በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት 1.5 ሚሊዮን አዳዲስ ተመጣጣኝ መኖሪያ ቤቶችን ለመገንባት መንግሥት አጠቃላይ ዝግጅት አድርጎ እየሠራ እንደሚገኝ አመልክተዋል።
አሁን ላይ አዲስ የግንባታ ቴክኖሎጂንና የረጅም ጊዜ የቤት ብድር ሥርዓትን በማስተዋወቅ የዜጎችን የቤት ባለቤትነት ጥያቄ በዘላቂነት ለመመለስ እየተሠራ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
አዲሱ የቤት ልማት ፖሊሲ ተቀርጾ በካቢኔ መጽደቁንና በሁሉም ክልሎች የተቀናጀ ንቅናቄ መጀመሩን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ግንባታው በመንግሥት በጀት ብቻ የሚወሰን ሳይሆን፣ የግሉ ዘርፍ እንዲሁም የመንግሥትና የግል አጋርነት መዋቅሮችን በስፋት መጠቀም እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
የዜጎችን የመግዛት አቅም ያገናዘበና ፍላጎታቸውን የሚያስተናግድ አዲስ የፋይናንስ አሠራር መፈጠሩን ጠቅሰው፤ሰዎች ቤት በቀጥታ መግዛት ካልቻሉ በመንግሥት በሚመቻቸው አዲስ የሞርጌጅ ሥርዓት አማካኝነት ከገቢያቸው ላይ እየከፈሉ በረጅም ጊዜ ሂደት የቤት ባለቤት የሚሆኑበት ዕድል ይፈጠራል ብለዋል።
ይህ ግብ የዜጎችን የቤት ፍላጎት ከማሟላት ባለፈ የግሉን ዘርፍ በስፋት በማሳተፍ የሚሳካ መሆኑ በግልጽ ተቀምጧል።
የሞርጌጅ ሥርዓት የቤት ፍላጎትን ለማሟላት የቀረበ ሌላኛው አማራጭ ሆኗል።
የቤት መግዣ ብድር ሥርዓት (ሞርጌጅ) ማለት አንድ ግለሰብ መኖሪያ ቤት ለመግዛት የሚያስፈልገውን ገንዘብ ከባንክ በብድር አግኝቶ፣ ያንን የተበደረውን ገንዘብ ከነወለዱ በረጅም ዓመታት መልሶ የሚከፍልበት የፋይናንስ አሠራር ነው።
ይህ አሠራር አቅማቸው ውስን ለሆኑ ዝቅተኛና መካከለኛ ገቢ ያላቸው ዜጎች በወር በወር እየከፈሉ የቤት ባለቤት የመሆን ልዩ ዕድል ይፈጥራል። የከፍተኛ የቤት ኪራይ ወጪን በማስቀረት ዜጎች በየወሩ የሚከፍሉት ገንዘብ በራሳቸው ንብረት ላይ የሚደረግ ጠቃሚ ኢንቨስትመንት እንዲሆን ያደርጋል።
ይህንን ታላቅ ራዕይ ከግብ ለማድረስ በዓለም አቀፉ የፋይናንስ ኮርፖሬሽን (IFC) እና በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ መካከል በሀገሪቱ የመጀመሪያው የቤት መግዣ ብድር መልሶ ማጠናከሪያ ኩባንያ ለማቋቋም የሚያስችል ታሪካዊ ስምምነት ተፈጽሟል።
በ100 ቢሊዮን የኢትዮጵያ ብር ካፒታል የተቋቋመው እና በዓለም አቀፍ የፋይናንስ ኮርፖሬሽን ደግሞ 200 ሚሊዮን ዶላር የሚደርስ አስተዋፅዖ የሚያደርግበት ይህ ተቋም፤ በባንክ ዘርፉ ውስጥ የጥሬ ገንዘብ ፍሰት አለመመጣጠንን የሚቀርፍ እና በመላው ኢትዮጵያ ተደራሽ የሚሆን የቤት መግዣ ብድር ፋይናንስን የሚያስገኝ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በመልዕክታቸው ገልጸዋል።
ይህ አጋርነት በተመጣጣኝ ዋጋ የሚገነቡና የኢትዮጵያውያንን ክብር የጠበቁ 1.5 ሚሊዮን ቤቶችን ለማቅረብ እንዲሁም በፋይናንስ ሥርዓታችን ውስጥ የግል ዘርፉን ተሳትፎ ለማስፋት የተቀመጠውን ግብ የሚያሳካ ወሳኝ እርምጃ መሆኑንም ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ ፈጣን፣ ጠንካራ እና ሁሉንም ያካተተ ኢኮኖሚ መገንባቷን እንደምትቀጥልም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።
የዓለም አቀፉ የፋይናንስ ኮርፖሬሽን (IFC) ማኔጂንግ ዳይሬክተር ማክታር ዲዮፕ በሰጡት አስተያየት፣ ይህ አጋርነት በኢትዮጵያ የከተሞች ልማት ላይ የግል ባለሀብቶች በስፋት እንዲሳተፉ ትልቅ ምቹ ምህዳር እንደሚፈጥር ገልጸዋል።
ጠንካራ የቤት ፋይናንስ ገበያ የዜጎችን ሕይወት ለማሻሻል እና የኢኮኖሚ ዕድገትን ለመደገፍ ቁልፍ መሆኑንም አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉዳዩ እንዲጀመር እንዲሁም ሂደቱ ላይ ክትትል በማድረግ እያከናወኑት ላለው ሥራና አመራር ማኔጂንግ ዳይሬክተሩ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
በዚህ የፋይናንስ ማዕቀፍ አማካኝነት ዜጎች ሙሉ የቤት መግዣ ገንዘብ እስኪኖራቸው ሳይጠብቁ በባንክ ብድር የቤት ባለቤት እንዲሆኑ ይደረጋል።ግንባታው በመንግሥት በጀት ብቻ ሳይሆን በመንግሥት፣ በግል ዘርፍ፣ እንዲሁም በመንግሥትና በግል አጋርነት (PPP) ይከናወናል።
የሞርጌጅ ፋይናንስ ሥርዓቱ የዜጎችን ማህበራዊ ዋስትና በማረጋገጥ የባለቤትነት ስሜት ከመፍጠር አኳያ ያለው ፋይዳ ቁልፍ የሚባል ነው።
መንግሥት ብቻውን ሊያከናውነው የሚችለውን ግዙፍ የልማት ጫና፣የግሉን ዘርፍ እና ዓለም አቀፍ አጋሮችን በማስተባበር በጋራ መወጣት እንደሚቻል የዛሬው ስምምነት ግልጽ ማሳያ ነው።
የ100 ቢሊዮን ብር ካፒታል ፈንድ እና የ1.5 ሚሊዮን ቤቶች ዕቅድ እውን መሆን፣ የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ጉዞ የሚያፋጥንና ሁሉንም ዜጎች አካታች የልማት ባለቤት የሚያደርግ ታሪካዊ ምዕራፍ ነው።