በሸገር ከተማ እየተካሄደ ያለው የበጎ ፍቃድ አገልግሎት የልማት ስራዎችን እያፋጠነ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በሸገር ከተማ እየተካሄደ ያለው የበጎ ፍቃድ አገልግሎት የልማት ስራዎችን እያፋጠነ ነው
ሸገር፣ ነሐሴ 29/2018(ኢዜአ)፡- በሸገር ከተማ እየተከናወነ የሚገኘው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የከተማ አስተዳደሩን ከፍተኛ የፋይናንስ ወጪ በማዳን የተለያዩ የልማት እንቅስቃሴዎችን ለማፋጠን ማስቻሉን የከተማው የገንዘብ ጽሕፈት ቤት ገለጸ።
የሸገር ከተማ አስተዳደር የሚነሱ ሰፊ የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማት ፍላጎቶችን በመንግሥት መደበኛ የበጀት አቅም ብቻ ማሟላት የማይቻል በመሆኑ፣ የኅብረተሰቡንና የልዩ ልዩ አካላትን ጉልበት፣ እውቀትና ሀብት ባቀናጀ መልኩ ማስተባበር አስፈላጊ ሆኗል።
በዚህም መሠረት በከተማ ደረጃ የሚካሄዱ የበጎ ፈቃድ አገልግሎቶች በዋናነት የአቅመ ደካሞችን ቤት ማደስ፣ የችግኝ ተከላና የአካባቢ ጥበቃ፣ የማህበረሰብ ጤናና ትምህርት ድጋፎች እንዲሁም የተለያዩ የመሠረተ ልማት ሥራዎችን ትኩረት አድርገው ሲከናወኑ ቆይተዋል።
እነዚህ ተግባራት በመደበኛ የጨረታና ኮንትራት አሰራር ቢፈጸሙ ኖሮ ከከተማው ካፒታልና መደበኛ በጀት ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቁ ነበሩ።
አሁን ላይ የበጎ ፈቃደኞችን፣ የወጣቶችንና የባለሀብቶችን ተሳትፎ በማጎልበት የተካሄዱት እንቅስቃሴዎች የከተማዋን በጀት ከመቆጠባቸው ባሻገር፣ የተመደበውን ውስን የመንግሥት ሀብት ለሌሎች ቅድሚያ ለሚሰጣቸው ታላላቅ የልማት ፕሮጀክቶች ለማዋልና የአገልግሎት ተዳራሽነትን ለማፋጠን ማስቻላቸው ተገልጿል።
የከተማ አስተዳደሩ ገንዘብ ጽሕፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ ወርቅነህ ድሳሳ ለኢዜአ እንደገለጹት፣ የተከናወነው የተቀናጀ የክረምት የበጎ ፈቃድ እንቅስቃሴ አበረታች ውጤቶችን ማስመዝገቡን ገልጸው፤ መርሃ ግብሩ ስኬታማ በሆነ መንገድ እየተካሄደ ይገኛል።
በመንግሥት የበጀት አቅም ብቻ ሊሸፈኑ የማይችሉ ሰፋፊ የልማት ተግባራት በበጎ ፈቃድ እንቅስቃሴው መከናወናቸውን ያብራሩት አቶ ወርቅነህ፣ ይህም በከተማዋ የሚኖሩ ድጋፍ ፈላጊ ወገኖችን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጫናዎች ለማቃለል ትልቅ አስተዋፅኦ ማበርከቱን ተናግረዋል።
በበጎ ፈቃድ እንቅስቃሴው ባለፈው የበጀት ዓመት ከታቀደው በላይ ከፍተኛ አፈጻጸም መመዝገቡን ያብራሩት አቶ ወርቅነህ፣ በዚህም የ25 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ተግባራት ለማከናወን ታቅዶ 28 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ግምት የሚያወጣ የልማትና የድጋፍ ሥራ ማከናወን መቻሉን ገልጸዋል።
በያዝነው የበጀት ዓመትም በ105 የሥራ ዘርፎች 29 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር ግምት ያላቸው የበጎ ፈቃድ ሥራዎችን ለማከናወን ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን አቶ ወርቅነህ ጠቁመዋል።
የበጎ ፈቃድ እንቅስቃሴው በርካታ የልማት ተግባራትን በአጭር ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ ያስቻለ መሆኑን ያብራሩት አቶ ወርቅነህ፣ ይህም ሕዝብንና መንግሥትን ሁለንተናዊ በሆነ መልኩ ከማገዙ ባሻገር ፈጣንና ዘላቂ ለውጥ ለማምጣት ትልቅ አቅም መፍጠሩን አስረድተዋል።
ማዕድ የማጋራት፣ የችግኝ ተከላና የአካባቢ ጥበቃ ሥራዎችን ጨምሮ የመጠጥ ውሃ፣ የድልድይ፣ የጠጠርና ኮብልስቶን መንገድ ግንባታ እንዲሁም የአቅመ ደካሞችን ቤት የማደስና የመገንባት ተግባራት በሰፊው እየተከናወኑ እንደሚገኙ አስረድተዋል።
በበጎ ፈቃድ እንቅስቃሴው የተሳኩት የልማት ሥራዎች የከተማውን መደበኛ በጀት ከመታደጋቸው ባሻገር፣ አስተዳደሩ የፋይናንስ አቅሙን ለሌሎች ቅድሚያ ለሚሰጣቸው ተጨማሪ የልማት ፕሮጀክቶች እንዲያውል ትልቅ ዕድል መፍጠራቸውን አቶ ወርቅነህ ገልጸዋል።