የመንግሥትን የሰላም ጥሪ ተቀብሎ ህዝብን መካስ ጀግንነትና የሀገር ወዳድነት መገለጫ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የመንግሥትን የሰላም ጥሪ ተቀብሎ ህዝብን መካስ ጀግንነትና የሀገር ወዳድነት መገለጫ ነው
መተማ፤ ነሐሴ29/2018(ኢዜአ) ፦ የመንግሥትን የሰላም ጥሪ ተቀብሎ ህዝብን መካስ ጀግንነትና የሀገር ወዳድነት መገለጫ ነው ሲሉ ኢዜአ ያነጋገራቸው የኃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች ገለጹ።
በተለያዩ አካባቢዎች አሁንም በጫካ የሚገኙ የታጠቁ አካላት ለመንግስት የሰላም ጥሪ ፈጣን ምላሽ በመስጠት እድሉን በአግባቡ ሊጠቀሙበት እንደሚገባ መክረዋል።
በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ትጥቅ ይዘው በየጫካው ይንቀሳቀሱ የነበሩ ታጣቂዎች የመንግስትን የሰላም ጥሪ በመቀበል ትጥቃቸውን በመፍታት ማህበረሰቡን መቀላቀላቸውን ቀጥለዋል።
በተሳሳተ መንገድ በትጥቅ እንቅስቃሴ የነበሩ በርካታ ወጣቶች እውነታውን በመረዳት በህዝብ ላይ እገታና ዘረፋ አንፈፅምም በማለት የሰላም ጥሪውን ተቀብለው እየመጡም ነው።
በዚሁ ጉዳይ ላይ አስተያየታቸውን የሰጡ የኃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች የመንግስትን የሰላምን ጥሪ በመቀበል ከጥፋት መንገድ እየወጡ ያሉ ታጣቂዎች አርአያነት ያለው ተግባር እየፈፀሙ መሆኑን ገልጸው ሌሎችም ይህንኑ መልካም መንገድ እንዲከተሉ መክረዋል።
የመንግሥትን የሰላም ጥረትና ቁርጠኝነት በማድነቅ የታጠቁ አካላት ይህንን መልካም እድል በመጠቀም ትጥቃቸውን በመፍታት ለሰላምና ልማት መዘጋጀት አለባቸው ብለዋል።
በምእራብ ጎንደር ዞን በመተማ ወረዳ የሚኖሩት የኃይማኖት አባት ሊቀ ህሩያን እያሱ ገዳሙ እና መጋቤ ብርሃን ዘላለም አዲሱ፤ የመንግስት ሆደ ሰፊነትና ለሰላም የሚያደርገውን ተደጋጋሚ ጥረት አድንቀዋል።
በዚህም መሰረት የመንግሥትን የሰላም ጥሪ በመቀበል ከጥፋት መንገድ እየወጡ ያሉ ታጣቂዎች አርአያነት ያለው ተግባር እየፈፀሙ መሆኑን አንስተው ሌሎችም ይህንኑ ፈለግ እንዲከተሉ መክረዋል።
በጫካ የሚገኙ ታጣቂዎች ተጨማሪ ህይወት ሳይጠፋና ንብረት ሳይወድም የተሰጠውን የሰላም እድል በመጠቀም ለህዝባቸው እፎይታን መስጠት እንዳለባቸው አሳስበዋል።
የሀገር ሽማግሌው አቶ ደርቤ ጫኔ፤ ለሰላም የሚደረግ ጥረት ጀግንነትና ቁርጠኝነትን የሚጠይቅ መሆኑን ገልጸው ለመንግስት ተደጋጋሚ የሰላም ጥረትና ሰላምን መርጠው እየመጡ ላሉ ታጣቂዎች አመስግነዋል።
በመሆኑ በጫካ የቀሩ ታጣቂዎች የህዝቡን ፍላጎትና የመንግሥትን የሰላም ጥረት ትርጉም በመስጠት ከጥፋት ወጥተው ሰላምን መርጠው ህዝቡን እንዲቀላቀሉ ጠይቀዋል።
በመሆኑም ይቅር ባይነትን በማስቀደም ወደ ሰላም መንገድ መመለስ እና ይህንን እድል መጠቀም ለህዝብና ለሀገር በማሰብ የሚፈፀም በመሆኑ የሰላም ቁርጠኝነት ማሳያ ነው ብለዋል።