ቀጥታ፡

በበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ ማህበራዊ ችግራችን ተቃሏል-በአምቦ ከተማ የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች

አምቦ፤ ነሐሴ 29/2018(ኢዜአ)፡- በክረምቱ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የተደረገላቸው ድጋፍ ማህበራዊ ችግራቸውን እንዳቃለለላቸው በአምቦ ከተማ የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች ተናገሩ።

በኢትዮጵያ በየዓመቱ የሚካሄደው የክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በዋናነት አቅመ ደካሞችን፣ አረጋውያንን እና አነስተኛ ገቢ ያላቸውን የህብረተሰብ ክፍሎች በዘላቂና በጊዜያዊ ድጋፎች ለማገዝ የሚከናወን አገር አቀፍ እንቅስቃሴ ነው።

በአምቦ ከተማም በበጎ ፈቃደኛ ወጣቶች፣ በባለሙያዎችና በባለሀብቶች አስተባባሪነት በየክረምቱ የሚከናወኑት የቤት እድሳት፣ የምግብና የቁስ ድጋፍ፣ የማጠናከሪያ ትምህርት እንዲሁም የነፃ ህክምና አገልግሎቶች የብዙ ነዋሪዎችን የኑሮ ጫና ሲያቃልሉ ቆይተዋል።

ኢዜአ ያነጋገራቸው የአምቦ ከተማ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተጠቃሚዎች ለረጅም ዓመታት ያረጁ የመኖሪያ ቤቶች ውስጥ በመኖራቸው ለከፍተኛ ችግር ተጋልጠው እንደነበር አንስተዋል።

አሁን ላይ አዲስ ቤት ተሰርቶላቸው የተሟላ ኑሮ መኖር መጀመራቸውን ይገልጻሉ።

ከነዋሪዎቹ መካከል አቶ ዘውዴ ደበሌ ይኖሩበት የነበረው ቤት ከክረምት ዝናብም ሆነ ከበጋ ፀሐይ የማይከላከልላቸው እንደነበር ጠቅሰው፤ ይህም ለከፍተኛ ችግር ዳርጓቸው እንደቆየ ተናግረዋል።

በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ቤታቸው እንደ አዲስ መገንባቱ በመጀመሩ መደሰታቸውን ተናግረዋል።

የበጎ ፈቃድ እንቅስቃሴው ህብረተሰቡ የነበረውን ጥንታዊ የመረዳዳትና የመደጋገፍ ዕሴት እንደገና የሚያነቃቃ በመሆኑ በስፋት ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባም ጠቁመዋል።

ባጋጠማቸው የአካል ጉዳት ሰርተው  ልጆቻቸውን የማስተዳደር አቅማቸው ተዳክሞ በችግር ውስጥ መቆየታቸውን የተናገሩት ደግሞ ሌላኛው የአገልግሎቱ ተጠቃሚ አቶ ኤቢሳ አብዲሳ ናቸው።

ሊፈርስ ከደረሰ ቤት ውስጥ በስጋት ይኖሩ እንደነበር ያነሱት አቶ ኤቢሳ፣ የከተማው አስተዳደር በበጎ ፈቃድ አገልግሎት አዲስ ቤት ሰርቶ በመስጠቱ በአሁኑ ወቅት ከተጋረጠባቸው ስጋት መላቀቃቸውን ተናግረዋል።

የአምቦ ከተማ ገንዘብ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ታምራት ሙለታ በበኩላቸው በዘንድሮው የክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት 59 የሥራ ዘርፎች ተለይተው ወደ እንቅስቃሴ መገባቱን ገልጸዋል። 

በነዚህ ተግባራትም ወጣቶችን ጨምሮ የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች በንቃት እየተሳተፉ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

በበጎ ፈቃድ እንቅስቃሴው በአጠቃላይ 91 ሺህ 529 የኅብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ለማድረግ ታቅዶ እየተሠራ መሆኑን አስረድተዋል።

በበጎ ፈቃድ ዘመቻው ፣ የአቅመ ደካሞችን ቤት ከማደስና ከመገንባት ጀምሮ የጤና፣ የትምህርት፣ የአካባቢ ጥበቃና የግብርና ሥራዎች በዋናነት እየተከናወኑ እንደሚገኙ አስረድተዋል።

በክረምቱ የበጎ ፈቃድ ዘመቻ የኅብረተሰቡን ሁለንተናዊ ተሳትፎ ማሳደግ መቻሉን የጠቀሱት ሃላፊው፤ በዚህም 255 ሚሊዮን 181 ሺህ 448 ብር የሚገመቱ የተለያዩ የማህበረሰብ ልማትና የድጋፍ ሥራዎች መከናወናቸውን አረጋግጠዋል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም