ሊቨርፑል በሊጉ የመጀመሪያ ድሉን ለማግኘት ከኤፕስዊች ታውን ጋር ይጫወታል - ኢዜአ አማርኛ
ሊቨርፑል በሊጉ የመጀመሪያ ድሉን ለማግኘት ከኤፕስዊች ታውን ጋር ይጫወታል
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 29/2018 (ኢዜአ):- የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የሶስተኛ መርሐ ግብር ዛሬ ይጀመራል።
ምሽት አራት ሰዓት ላይ ኤፕስዊች ታውን ከሊቨርፑል በፖርትማን ሮድ ስታዲየም ይጫወታሉ።
ከሁለት የሊጉ ጨዋታዎች ሶስት ነጥብ ያገኘው ኤፕስዊች ታውን 12ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
ተጋጣሚው ሊቨርፑል በሁለት ነጥብ 13ኛ ደረጃን ይዟል።
ሁለቱ ክለቦች በሊጉ ሲገናኙ የአሁኑ ለ13ኛ ጊዜ ነው።
ከዚህ ቀደም ባደረጓቸው 12 ጨዋታዎች ሊቨርፑል ሰባት ጊዜ ሲያሸንፍ ኤፕስዊች ታውን ሁለት ጊዜ ድል ቀንቶታል። በቀሪ ሶስት ጨዋታዎች አቻ ተለያይተዋል።
ሊቨርፑል በ12 ጨዋታዎች ላይ 26 ግቦችን ከመረብ ላይ ሲያሳርፍ ኤፕስዊች ታውን ዘጠኝ ጎሎችን አስቆጥሯል።
ክለቦቹ በፕሪሚየር ሊጉ ለመጨረሻ ጊዜ የተገናኙት እ.አ.አ ጃንዋሪ 2025 ሲሆን በአንፊልድ ሮድ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ ሊቨርፑል 4 ለ 1 ማሸነፉ የሚታወስ ነው።
ባለሜዳው ኤፕስዊች ታውን በሁለተኛ ሳምንት በማንችስተር ዩናይትድ ካጋጠመው የ5 ለ 2 ሽንፈት አገግሞ ወደ አሸናፊነት ለመመለስ ወደ ሜዳ ይገባል።
በሁለቱም የሊጉ ጨዋታዎች አቻ የወጣው ሊቨርፑል የመጀመሪያ ድሉን ለማስመዝገብ ይፋለማል።
የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የሶስተኛ መርሐ ግብር እስከ ጳጉሜን 1 ቀን 2018 ዓ.ም ይቆያል።