የኮሪደር ልማት እና የነገዋ ኢትዮጵያ - ኢዜአ አማርኛ
የኮሪደር ልማት እና የነገዋ ኢትዮጵያ
በኢትዮጵያ አሁን ላይ በተለያዩ መስኮች እየተከናወኑ ያሉ ስራዎች መጻኢውን ጊዜ ብሩህ ለማድረግ መሰረት የሚጥሉ ናቸው።
ከእነዚህ ስራዎች በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀሰው የሀገሪቱን ከተሞች ገጽታና የነዋሪዎቿን የኑሮ ዘይቤ በከፍተኛ ደረጃ እየቀየረ ያለው የኮሪደር ልማት መርሃ ግብር ነው።
ይህ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሀሳብ አመንጪነት የተጀመረው የኮሪደር ልማት ከተሞችን ለኑሮ ምቹ፣ ንጹህና ስልጡን በማድረግ ትልቅ ምዕራፍ ከፍቷል።
በአጭር ጊዜ ውስጥ ያስመዘገበው ስኬትና የፈጠረው አርአያነት አሁን ላይ አዲስ አበባን አልፎ በኢትዮጵያ የተለያዩ ከተሞች ተግባራዊ ተደርጓል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በአንድ ወቅት እንደገለጹት፣ የኮሪደር ልማት ከከተማ ውበትና ገጽታ ባለፈ የሀገሪቱን የዕድገት አቅጣጫ በከፍተኛ ደረጃ እየቀየረ ያለ እና የነገዋን ሀገር ዛሬ ላይ የመቅረጽ ስትራቴጂካዊ እርምጃ ነው።
በኮሪደር ልማቱ ለእግረኛ እና ለአካል ጉዳተኞች ፈታኝ የነበሩ መንገዶች ዛሬ ሰፊና ጥራት ባላቸው የኮንክሪት ንጣፎችና የብስክሌት መስመሮች ተተክተዋል።
በከተሞች የሚገኙ የመዝናኛ ፓርኮች፣ የማረፊያ ስፍራዎች እንዲሁም ደረጃቸውን የጠበቁ ቦታዎች የዜጎችን ማኅበራዊና ሰብአዊ ክብር ከፍ ያደረጉ ሲሆን፤ እነዚህ ጥራት ያላቸው መሠረተ-ልማቶች የነገውን ጤናማ እና ማህበራዊ ፍትሕ የሰፈነበት ማህበረሰብ ለመፍጠር የተጣሉ ጠንካራ መሠረቶች ናቸው።
የኮሪደር ልማት የከተሞችን የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ወደ ዘመናዊነት በመቀየር ረገድ ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ ይገኛል።
በዘመናዊ የጎዳና ላይ መብራቶችና የደህንነት ካሜራዎች የታገዙ ከተሞች በቀን ብቻ ሳይሆን በሌሊትም የንግድና የኢኮኖሚ ማዕከል እንዲሆኑ በር በመክፈታቸው፣ የ24 ሰዓት የስራ ባህልን በመፍጠር ለአያሌ ወጣቶችና አነስተኛ ነጋዴዎች አዲስ የሥራ ዕድል ፈጥረዋል።
በሌላ በኩል፣ ይህ ስትራቴጂካዊ ልማት ኢትዮጵያን ወደ ቋሚ የኮንፈረንስ፣ የንግድ እና የባህል ቱሪዝም መዳረሻነት እየቀየራትም ይገኛል።
በተለይም የከተሞችን ማህበራዊ መስተጋብርና የሕዝቡን አንድነት በማጠናከር ረገድ የኮሪደር ልማቱ እያበረከተ ያለው አስተዋጽኦ የላቀ ነው።
በልማቱ የተፈጠረው የጋራ ትስስር የነገዋን ጠንካራ፣ ሰላማዊና በአብሮነት የታነጸች ሀገር ለመገንባት እንደ ትልቅ ማህበራዊ መሰረት ያገለግላል።
የነገዋ ኢትዮጵያ በዲጂታል ቴክኖሎጂ አቅም ያደገችና አሰራሯ የዘመነ መሆኑን የሚያረጋግጥ ተግባራዊ እርምጃ ከኮሪደር ልማቱ ጋር ተሳስሮ ተግባራዊ መደረግ ጀምሯል።
ስራው ከቴክኖሎጂ ተቋማት ጋር በቅንጅት በማከናወን ዘመናዊ የትራፊክ ቁጥጥር ሥርዓቶች እና የስማርት ከተማ መተግበሪያዎች መሰረተ ልማት አብሮ እየተዘረጋ ይገኛል።
በተጨማሪም ከኮሪደር ልማት ጋር እየተከናወነ ያለው መጠነ ሰፊ የአረንጓዴ ስፍራዎች እና የወንዞች ዳርቻ ልማቶች ከተሞች ከአየር ንብረት ለውጥ ስጋትና ሙቀት በመከላከል ለትውልዱ ንጹህና ጽዱ መኖሪያን አካባቢን ለማስረከብና ጤናማ ማህበረሰብ ለመገንባት እያስቻለ ነው።
በአጠቃላይ የኮሪደር ልማት ፕሮጀክት ከአንድ ከተማ ገጽታ ማሻሻል ባሻገር፣ በመላ ሀገሪቱ በሚገኙ በርካታ ክልል ከተሞች ላይ በመስፋፋት ሀገራዊ ለውጥ ፈጥሯል ማለት ያስችላል።
የዚህ ዘርፈ ብዙ የልማት ፍሬ ዛሬ ላይ የኑሮ ዘይቤን እያሻሻለ እንደሚገኘው ሁሉ፣ ለወደፊቱ ትውልድም የኩራት ምንጭ የሆነ ዘላቂ ሀብት ሆኖ ይሸጋገራል።
ዛሬ በጥራትና ውብ ሆነው እየተሰሩ ያሉ መንገዶች፣ ዘመናዊ መናፈሻዎች፣ የህጻናት መጫወቻ ስፍራዎች፣ የስፖርት ማዘውተሪያዎች እና የዲጂታል መሰረተ ልማቶች የነገዋ ኢትዮጵያ የበለጸገች፣ ስልጡንና ለኑሮ ምቹ የማድረግ ራዕይን እውን የሚያደርጉ ናቸው።