የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ያስገነባው የፍትሕ ሙዚየም ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት ሆነ - ኢዜአ አማርኛ
የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ያስገነባው የፍትሕ ሙዚየም ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት ሆነ
ባህር ዳር ነሐሴ 28/2018;(ኢዜአ) ፦ የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ያስገነባው የፍትሕ ሙዚየም በርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት ሆነ።
ርዕሰ መስተዳድሩ በዚሁ መርሃ ግብር ላይ ባደረጉት ንግግር የፍትህ ሙዚየም መገንባቱ የህዝቡን የፍትህ እሴትና በህግ የበላይነት ከማሳየት ባሻገር ተቋማት ለለውጥ ያላቸውን መነሳሳት የሚያመላክት መሆኑን ገልጸዋል።
በሀገሪቱ የፍትህ አስተዳደር ታሪክ ለጥናትና ምርምር የሚሆኑ ሰነዶችንና ሌሎች ቁሳቁሶችን የያዘ በመሆኑም ለአዲሱ ትውልድ እሴትና ተደማሪ የእውቀት ምንጭ ሆኖ የሚያገለግል ይሆናል ብለዋል።
በመሆኑም ይሄንን ታሪካዊ አሻራ ላስቀመጡና መረጃዎችን በማሰባሰብ ለምረቃ እንዲበቃ ላደረጉ የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ አመራሮችና ባለሙያዎችም ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት መንገሻ አየነ (ዶ/ር)፤ የሙዚየሙ መገንባት በተለይም ለዩኒቨርሲቲው ተማሪዎችና ተመራማሪዎች ትልቅ እሴት የሚሆን ነው ብለዋል።
በካታሎግና በዲጂታል ቴክኖሎጂ የታገዘውን የአገራችን የፍትህ ታሪክ ተማሪዎች በቀላሉ እንዲያውቁና ለምርምር ግባአት እንዲጠቀሙበት የሚያስችል መሆኑንም አንስተዋል።
የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት አለምአንተ አግደው፤ ሙዚየሙ ከባህላዊ እስከ ዘመናዊ አስተዳደር የነበሩ የፍትህ ታሪኮችን ሰንዶ በመያዝ የተደራጀ መሆኑን ገልጸዋል።
በቀጣይም ለህግ ማሻሻያ፣ ለፖሊሲና ስትራቴጂ ቀረጻና ለሌሎችም የጥናትና ምርምር ስራዎች ትልቅ አቅምና ግብአት ይሆናል ብለዋል።
በሙዚየሙ ውስጥ ከ19ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ የነበሩና ሌላ ቦታ በቀላሉ ሊገኙ የማይችሉ ብርቅዬ የፍትህ ሰነዶች የሚገኙበት ነው ብለዋል።
እነዚህን ታሪካዊ መረጃዎች ከተለያዩ ቦታዎች ለማሰባሰብ ክልል አቀፍ ኮሚቴ ተዋቅሮ ሰፊ ስራ መሰራቱን አንስተው አጠቃላይ የሙዚየሙ ግንባታ አላማ የህዝቡን የፍትህ ስርዓት ታሪክ በመጠበቅ ለቀጣዩ ትውልድ ለማስተላለፍ መሆኑን ተናግረዋል።
በፍትሕ ሙዚየም የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) ጨምሮ ሌሎችም የፌዴራልና የክልሉ ከፍተኛ የመንግሥት የስራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል።