ቀጥታ፡

ፅምዶ የጋራ ዓላማ የሌለውና የትም የማይደርስ ስብስብ ነው-ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ

አዲስ አበባ፤ነሐሴ 28/2018 (ኢዜአ)፦ ፅምዶ የጋራ ዓላማ የሌለውና የትም የማይደርስ ስብስብ መሆኑን አንጋፋው ፖለቲከኛ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ገለጹ።

አንጋፋው ፖለቲከኛ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ለኢዜአ በሰጡት ማብራሪያ፣ ኢትዮጵያ በረጅም ታሪኳ በውስጥ ችግሮችም ሆነ በውጭ ጣልቃ ገብነቶች የተዳከመች ብትመስልም በጽናትና በአሸናፊነት ያለፈች ሀገር መሆኗን አስታውሰዋል።

ኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅሟን የማሳካት ጉዞዋ በየትኛውም የጥፋት ጥምረት ሊከሽፍ የማይችል ጉዳይ መሆኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ፅምዶ በሚል የጋራ ዓላማ በሌለው ተራ የጥፋት ኃይሎች ስብስብም ሆነ ለሌሎች ትላልቅ ኃይሎች ጫና የምትበገር ጠንካራ ሀገር አለመሆኗን ገልጸው፤ ይህ በታሪኳም ሆነ በአሁናዊ ጉዞዋ የታየ ተጨባጭ ሀቅ ነው ብለዋል።

አሁን ፅምዶ በሚል የጥፋት ጥምረት የተሳሰቡት ኃይሎችም የጋራ ዓላማ የሌላቸውና አጭር ርቀት እንኳ አብረው መጓዝ የማይችሉና እርስ በርስ የሚጋጭ አጀንዳን ያነገቡ ተራ ስብስብ ናቸው ብለዋል።

እነዚህ ኃይሎች ወጣቶችን በማስገደድ ለእልቂት እየዳረጉ መሆናቸውን ጠቁመው፣ ቆመንልሃል የሚሉትን ህዝብ ለመከራ መዳረጋቸውን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያን ከጉዞዋ የሚያቆማት ኃይል የለም ያሉት ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ፤እነዚህ ትናንሽና አቅመ ቢስ ቡድኖች የጀመሩት የጥፋት መንገድም የትም እንደማያደርሳቸው ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም