ቀጥታ፡

በትምህርት ቤቶች የተጀመሩ የአካባቢ ጥበቃ ሥራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ

ሰመራ፤ ነሐሴ 28/2018 (ኢዜአ)፦ የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን ለመቀነስና ለመቋቋም በትምህርት ቤቶች የተጀመሩ የአካባቢ ጥበቃ ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የአፋር ክልል ትምህርት ቢሮ አስታወቀ።

በአየር ንብረት ለውጥና በአካባቢ ጥበቃ ሥራ ላይ የትምህርት ቤቶችን ሚና ለማሳደግ ያለመ የውይይት መድረክ ዛሬ በሰመራ ከተማ ተካሂዷል።

በመድረኩ የተገኙት የክልሉ ትምህርት ቢሮ ላፊ አቶ ሙሳ አደም እንዳሉት የአካባቢ እና የአየር ንብረት ለውጥ ጥበቃ ሥራ ዓለም አቀፍ ትኩረት ያለው ነው።

በዚህም የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን ለመቀነስና ለመቋቋም እንደ ሀገር የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብርን ጨምሮ የተለያዩ ስራዎች በመከናወን ላይ መሆናቸውን አንስተዋል።

የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን ለመቀነሰና ለመቋቋም በክልሉ በትምህርት ቤቶች የተጀመሩ ሥራዎችም ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።

በተለይም በክልሉ በረሃማ አካባቢዎች ለሚሰሩ የአካባቢ ጥበቃና የአየር ንብረት ለውጥ ሥራዎች ትምህርት ቤቶች ላይ ያተኮረ ስራ በስፋት እንደሚሰራ አስታውቀዋል።

የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን ለመከላከል በትምህርት ቤቶች ከአረንጓዴ አሻራ ልማት ሥራዎች በተጨማሪ የጓሮ እርሻ ሥራዎች በቅንጅት እየተከናወኑ መሆናቸውን አስረድተዋል።

በትምህርት ቤቶች ግቢ ውስጥ ከ100 ሺህ በላይ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው የተለያዩ ችግኞችን በመትከል አረንጓዴ እንዲላበሱ እየተደረገ መሆኑን ገልፀዋል።

በክልሉ ከዚህ ቀደም ብዙም ያልተለመደው የጓሮ እርሻ ልማትም በአሁኑ ወቅት እየተስፋፋና በ35 ትምህርት ቤቶችም ልማቱ እየተከናወነ መሆኑን በአብነት ጠቅሰዋል።


 

በመድረኩ ላይ የተገኙት በትምህርት ሚኒስቴር የትምህርት ፕሮግራሞችና ጥራት ማሻሻል መሪ ሥራ አስፈጻሚ ዮሐንሰ ወጋሶ (ዶ/ር) በበኩላቸው እንዳሉት፣ ትምህርት ቤቶች ከንድፈ ሀሳብ በተጨማሪ ተግባራዊ የመማማሪያ መስክ እንዲሆኑ ካለፉት ስድስት ዓመታት ጀምሮ በትኩረት እየተሰራ ነው።

ቅድመ መደበኛን ጨምሮ በአገር አቀፍ ደረጃ ከ56 ሺህ በላይ ትምህርት ቤቶች እንዳሉ ጠቅሰው፣ ከነዚህ ውስጥ በ24 ሺህ ትምህርት ቤቶች የጓሮ እርሻ ሥራ እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል።

የጓሮ እርሻ ማልማት የጀመሩና የተለያየ ጥቅም የሚሰጡ ችግኞችን የተከሉ ትምህርት ቤቶች ለአየር ንብረት ለውጥ መከላከል አዎንታዊ ሚና እየተጫወቱ ናቸው ብለዋል።

በመርሃ ግብር ላይ የተገኙት የአይሳኢታ ከተማ ትምህርት ጽህፈት ቤት ባለሙያ አቶ ፈንታው ካሳ በትምህርት ቤቶች ውስጥ በተሰሩ ሥራዎች ለውጥ መጥቷል።

በትምህርት ቤቶች ባዶ በነበረ ቦታ ላይ የተለያዩ ቋሚ ተክሎችን በመተከላቸው የአካባቢው ሞቃታማ የአየር ፀባይ እየተለወጠ መምጣቱን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም