ቀጥታ፡

የጳጉሜን ቀናት የመደመር መንግሥት ባስመዘገባቸው ውጤቶች በመታገዝ ለሌላ ስኬት በሚያዘጋጅ መልኩ ይከበራሉ - ከንቲባ ከድር ጁሃር

ድሬዳዋ ፤ ነሐሴ 28/2018(ኢዜአ) ፦ የጳጉሜን ቀናት በተለያዩ መርሃ ግብሮች ለማክበር ዝግጅት መደረጉን የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃር ገለጹ።

ከንቲባው በጳጉሜን አምስት ቀናት በሚከናወኑ መርሃ ግብሮች፣ እቅዶችና ዝግጅቶች ዙሪያ ዛሬ በሰጡት መግለጫ ቀናቱ የመደመር መንግሥት ባስመዘገባቸው ውጤቶች በመታገዝ ለሌላ ስኬት በሚያዘጋጅ መልኩ በተለያዩ ተግባራት ይከበራሉ ብለዋል።

በዚሁ መሠረት በጳጉሜን 1 የእመርታ ቀን እስካሁን የተከናወኑ ውጤታማ ሥራዎችን በላቀ ደረጃ ለማስቀጠል የሚያስችሉ ሁነቶች እንደሚካሔዱ ነው የገለጹት።

እስካሁን የተገኙ ድሎችን በተባበረ ቅንጅት ለማስቀጠልና ቀጣይነታቸውን ለማረጋገጥ በሚያስችሉ መርሃ ግብሮች የሚከበረው ደግሞ ጳጉሜን 2 የማንሰራራት ቀን ነው ብለዋል።

ጳጉሜን 3 የሚከበረው የጽናት ቀን የሀገርን አንድነትና ልማት ለማጽናት ለሚተጉ የሀገር መከላከያ፣ የጸጥታና የፍትሕ ተቋማት ያለንን ደጀንነትና ድጋፍ በማረጋገጥ እንደሆነም ነው ያመለከቱት ።

ጳጉሜን 4 የህብር ቀን የድሬዳዋን የመደጋገፍ፣ የመረዳዳትና ሰው ተኮር ልማቶች በሚያስቀጥሉ እንዲሁም ህብረ ብሔራዊ አንድነትን በሚያጠናክሩ ተግባራት ይከበራል ብለዋል።

ጳጉሜን 5 የነገ ቀን ደግሞ የአዲሱ ዓመት ዋዜማ እንደመሆኑ መጠን ሀገራችን በቴክኖሎጂው ዘርፍ እያስመዘገበች የምትገኘውን የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ጉዞ በሚያጠናክሩ ሁነቶች እንደሚከበር ከንቲባው አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም