መንግሥት የዜጎችን ኑሮ ማሻሻልና ዘላቂ ብልጽግናን ማረጋገጥ ቀዳሚ አጀንዳው አድርጓል - የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት - ኢዜአ አማርኛ
መንግሥት የዜጎችን ኑሮ ማሻሻልና ዘላቂ ብልጽግናን ማረጋገጥ ቀዳሚ አጀንዳው አድርጓል - የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት
አዲስ አበባ ነሐሴ 28/2018 (ኢዜአ)፦ መንግሥት የዜጎችን ኑሮ ማሻሻልና ዘላቂ ብልጽግናን ማረጋገጥ ቀዳሚ አጀንዳው ማድረጉን የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ገለጸ።
አገልግሎቱ መንግሥት ሃገራዊ ሪፎርሞችን በመተግበር የሕዝብን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የገባውን ቃል ወደ ተግባር እየለወጠ ይገኛል ብሏል።
ኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥና የዜጎቿን ሕይወት ከፍ ለማድረግ በምታደርገው ያልተቋረጠ ርብርብ፣ የኢትዮጵያን የማንሰራራት ጉዞ የሚያበስሩ ታሪካዊ ምዕራፎች እውን እየሆኑ ይገኛሉ ብሏል።
መንግሥት ሕዝብን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ስልታዊ ፖሊሲዎችን በመንደፍና በመተግበር በኢኮኖሚውና በማኅበራዊው ዘርፍ ተጨባጭ ለውጦችን በማስመዝገብ ላይ እንደሚገኝ ገልጿል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ዛሬ ይፋ የተደረገው በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ እና በዓለም አቀፍ የፋይናንስ ኮርፖሬሽን (IFC) መካከል የተደረሰው ታሪካዊ ስምምነት የዚህ አበይት ርዕይ አንዱ ማሳያ ነው ሲልም አገልግሎቱ አብራርቷል።
በ100 ቢሊየን ብር ካፒታል የሚቋቋመውና ዓለም አቀፍ አጋርነትን ያካተተው የቤት መግዣ ብድር መልሶ ማጠናከሪያ ኩባንያ፣ በባንክ ዘርፍ ያለውን የጥሬ ገንዘብ ፍሰት አለመመጣጠን በመቅረፍ ለዜጎች አስተማማኝ የፋይናንስ አቅርቦት ይፈጥራል ብሏል።
አገልግሎቱ ይህ ታሪካዊ ስምምነት መንግሥት በተመጣጣኝ ዋጋ የኢትዮጵያውያንን ክብር የጠበቁ 1.5 ሚሊየን ቤቶችን ለማቅረብ ያስቀመጠውን ግብ በግንባር ቀደምትነት የሚያሳካ መሆኑን ገልጿል።
ስምምነቱ የዜጎችን የቤት ባለቤትነት ፍላጎት እውን በማድረግ ረገድ የሚታዩ ማነቆዎችን በመስበር፣ የበርካቶችን የዕለት ተዕለት ሕይወትና ማኅበራዊ ደኅንነት በአስተማማኝ ሁኔታ የሚያሻሽል የመንግሥት ቁርጠኝነትን ያረጋገጠ ቁልፍ ርምጃ መሆኑንም ጠቅሷል።
ይህ ስኬት ብቻውን የቆመ አይደለም፤ ባለፉት የለውጥ ዓመታት በኢኮኖሚ ማሻሻያ፣ በዲጂታል ትራንስፎርሜሽን እና በሜጋ ፕሮጀክቶች የተመዘገቡት የኢትዮጵያን የማንሰራራት ድሎች ቀጣይ ምዕራፍ አካል ነው።
የመደመር መንግሥት የግል ዘርፉን ተሳትፎ በስፋት በማካተትና የገበያ ሥርዓቱን በማዘመን አገራዊ የኢኮኖሚ አቅምን ማጠናከር የልማት ጉዞው መሠረት አድርጎ ቀጥሏል።
እንደ ሀገር እየተመዘገበ ካለው ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት ጋር ተያይዞ በሚፈጠር የዋጋ ግሽበት አነስተኛ ገቢ ያላቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች ላይ የሚደርሰውን ተጋላጭነት ለመቀነስ፣ መንግሥት በቢሊዮኖች የሚቆጠር በጀት በመመደብ በነዳጅ፣ በመሠረታዊ ፍጆታዎች እና በግብርና ግብአቶች ላይ ከፍተኛ ድጋፎችን እያደረገ ይገኛል።
ከዚህ የዕለት ኑሮ ማቃለያ ሥራ ባሻገር የዜጎችን ኑሮ በዘላቂነት ማሻሻልና ብልጽግናን ማረጋገጥ ቀዳሚ አጀንዳው አድርጎል። በዚህም ቃል በተግባር እየተለወጠ ፈጣን፣ ጠንካራ እና ሁሉንም ያካተተ ኢኮኖሚ የመገንባት ጽኑ ፍላጎቱ በሁሉም መስክ በተግባር እየተፈጸመ ቀጥሏል ብሏል።