በምዕራብ ወለጋ ዞን የሰፈነው ሰላም የልማት ሥራዎችን በተያዘው ጊዜ ለማጠናቀቅ አስችሏል - ኢዜአ አማርኛ
በምዕራብ ወለጋ ዞን የሰፈነው ሰላም የልማት ሥራዎችን በተያዘው ጊዜ ለማጠናቀቅ አስችሏል
ጊምቢ፤ ነሐሴ 28/2018 (ኢዜአ) ፦ በዞኑ የሰፈነው ሰላም የልማት ሥራዎችን በቅንጅት ለመስራትና በተያዘላቸው ጊዜ አጠናቆ ለአገልግሎት ለማብቃት ማስቻሉን የምዕራብ ወለጋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ተሊላ ተረፈ ገለጹ።
በዞኑ ዪብዶ ወረዳ በ148 ሚሊዮን ብር የተገነቡ የተለያዩ የልማት ሥራዎች ተመርቀው ለአገልግሎት ክፍት ሆነዋል።
ግንባታቸው ተጠናቆ ለአገልግሎት ከበቁ ፕሮጀክቶች ውስጥ ሁለተኛው ትውልድ ጤና ኬላ፣ የሀር ትል ማባዣ ማዕከል፣ የወረዳው የስብሰባ አዳራሽ፣ የመንገድ እና ሌሎች የልማት ሥራዎች ይገኙበታል ።
በፕሮጀክቶቹ ምረቃ ላይ የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ እንደተናገሩት፣ በዞኑ በህብረተሰቡ ተሳትፎ እና በፀጥታ አካላት ቅንጅት ሰላምን በማስፈን የልማት ስራዎች በተያዘላቸው ጊዜ ተገንብተው ለአገልግሎት እንዲበቁ እየተደረገ ነው።
በዚህም በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከ470 በላይ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን በመገንባት ለአገልግሎት ለማብቃት መቻሉን ገልጸዋል፡፡
በቀጣይም ሕብረተሰቡ የሰላም ግንባታና የልማት ሥራዎች ላይ ተሳትፎውን ይበልጥ እንዲያጠናክር ጠይቀዋል።
የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተከናወኑ የልማት ሥራዎች የብልፅግና ጉዞን ለማሳካት የሚያግዝ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የዪብዶ ወረዳ አስተዳደር አቶ ደጋጋ ሞሐመድ ናቸው።
በአካባቢው የሰፈነው ሰላም የልማት ፕሮጀክቶች ተጠናቀው ለአገልግሎት እንዲበቁ ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን የተናገሩት ደግሞ የዩብዶ ወረዳ ነዋሪ መምህር ተክሉ ተሾመ ናቸው።
ግንባታቸው ተጠናቅቆ ለአገልግሎት የበቁት መሠረተ ልማቶችም ረጅም ዕድሜ እንዲያገለግሉ የበኩላቸውን እንደሚወጡ ገልጸዋል።
በወረዳው የብዙ ጊዜ የልማት ጥያቄያቸው ምላሽ ማግኘቱ የሚበረታታ መሆኑንና ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት የገለጹት ደግሞ ወይዘሮ ክብቱ ጋዲሳ የተባሉ ነዋሪ ናቸው።
የአካባቢው የፀጥታ ችግር መፈታቱ በተለያዩ የልማት ሥራዎች ላይ በንቃት በመሳተፍ ተጠቃሚ እንዳደረጋቸውም ገልጸዋል።
በቀጣይም የልማት ሥራዎች በሚፈለገው ልክ እንዲከናወኑ ለአካባቢያቸው ዘላቂ ሰላም ዘብ በመቆም የበኩላቸውን ለመወጣት መዘጋጀታቸውን አረጋግጠዋል።