ቀጥታ፡

የዜጎች የሲቪልና ቤተሰብ ምዝገባ አገልግሎት የመንግስት አስተዳደርን ውጤታማ ለማድረግ የሚያግዝ ነው- ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ

ባሕር ዳር ፤ ነሐሴ 28/2018(ኢዜአ) ፦የዜጎች የሲቪልና ቤተሰብ ምዝገባ አገልግሎት ዘመናዊ የምዝገባ ስርአት የመንግስት አስተዳደርን ውጤታማ ለማድረግ የሚያግዝ መሆኑን የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ ገለጹ።

የክልሉ ሲቪልና ቤተሰብ ምዝገባ አገልግሎት የዘመናዊ ቴክኖሎጂ ምዝገባ ሲስተም የሚያስተዋውቅ መርሃ ግብር በባህር ዳር ከተማ ተካሂዷል።

በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት ርዕሰ መስተዳድሩ የዜጎች መረጃ ዘላቂነትና ታማኝነትን በሚያረጋግጥ መልኩ የተደራጀ የምዝገባ ሥርዓት ጠቀሜታው የላቀ መሆኑን ተናግረዋል።

የህዝብን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ የልማት ስራዎችን በተጨባጭ መረጃ ላይ መሰረት አድርጎ ለመስራት የሚያስችል መሆኑን አንስተው ምዝገባው ለፖሊሲ አውጪዎችና ሌሎች አገልግሎቶችን ተደራሽ ለማድረግ ይጠቅማልም ብለዋል።

በቴክኖሎጂ የታገዘ የምዝገባ ስርአት ጊዜን፣ ጉልበትንና ወጪን ከመቆጠብም ባለፈ የመንግሥትና የህዝብን አስተዳደራዊ ግንኙነት የሚያጠናክር መሆኑን አስረድተዋል።

በመሆኑም ከአገልግሎቱ የሚገኘው መረጃ የስራ ቅልጥፍናንና የህዝብን ፍትሃዊ የልማት ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ በመሆኑ ለላቀ ውጤታማነት ሁሉም ተባብሮ ሊሰራ እንደሚገባ አሳስበዋል።

የክልሉ ሲቪልና ቤተሰብ ምዝገባ አገልግሎት ኃላፊ ወይዘሪት መዓዛ በዛብህ፤ አገልግሎቱ በቴክኖሎጂ ታግዞ ተደራሽ መደረጉ ፈጣንና ደህንነቱ የተረጋገጠ ትክክለኛ መረጃን ጥቅም ላይ ለማዋል እንደሚረዳ ተናግረዋል።

በተጨማሪም ብልሹ አሰራርን፣ ሀሰተኛና ህገ-ወጥ ሰነዶችን ከመከላከል ባለፈ በትክክለኛና ተጨባጭ መረጃ ላይ ተመስርቶ ውጤታማ ስራዎችን ለማከናወን ያስችላል ብለዋል።

በተጠናቀቀው በጀት ዓመትም በ761 የምዝገባ ጣቢያዎች ከአንድ ሚሊዮን በላይ ኩነቶች መመዝገባቸውን ጠቅሰዋል።

በቀጣይም የዘርፉን የዲጂታል 2030 እቅድ እውን የማድረግ ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸው፣ ለዚህ ውጤታማነት የባለድርሻ አካላት ትብብርና ድጋፍ ወሳኝ መሆኑን አመላክተዋል።

በመድረኩ የክልሉ ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ፋንቱ ተስፋዬ፣ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ በለጠ ሞላን (ዶ/ር) ጨምሮ ሌሎች የክልል፣ የዞንና የከተማ አስተዳደር አመራሮች የተሳተፉ ሲሆን፣ በ2018 በጀት ዓመት አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላትም እውቅና ተሰጥቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም