የመደመር መንግሥት የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ ምሰሶዎች መካከል አንዱ የሆነው የቱሪዝም ዘርፍ ስኬቶች በሀረሪ ክልል - ኢዜአ አማርኛ
የመደመር መንግሥት የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ ምሰሶዎች መካከል አንዱ የሆነው የቱሪዝም ዘርፍ ስኬቶች በሀረሪ ክልል
የመደመር መንግሥት የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ ምሰሶዎች መካከል አንዱ የሆነውን የቱሪዝም ዘርፍ ለማሳደግ ውጤታማ ስራዎች ተከናውነዋል።
በተከናወኑ ተግባራት ተጨባጭና ትውልድን የሚሻገሩ ድሎች ማስመስገብ ከተቻለባቸው አካባቢዎች መካከል የሀረሪ ክልል ተጠቃሽ ነው።
የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ለቱሪዝም መዳረሻዎች ልማት በሰጡት ልዩ ትኩረት ዛሬን ተሻግሮ ለነገዋ ኢትዮጵያ ብልፅግና መሰረት የሚሆኑ ስራዎች ተከናውነዋል።
ከመደመር ትውልድ መፅሐፍ ሽያጭ በተገኘና የሀረሪ ክልል መንግሥት በመደበው ተጨማሪ በጀት በሀረር ከተማ እውን የተደረገው የሀረር ኢኮ ቱሪዝም ፖርክም ለዚህ አንዱ ማሳያ ነው።
የፓርኩ መገንባት ከዚህ ቀደም የህዝብና የጎብኚዎችን ደህንነት ባልጠበቀና የጅቦች ምቾት ባልጠበቀ መልኩ በየመንደሩ ሲካሄድ የቆየው የጅብ ትርኢት አሁን ላይ በዘመናዊ መልኩ እንዲደረግ ያስቻለ ሆኗል።
ፓርኩ የጅብ ትርዒቱን በተደራጀ መልኩ በአንድ ማዕከል እንዲካሄድ ከማድረግም ባሻገር አገር በቀልና መድኃኒትነት ያላቸው እፅዋቶችን ጨምሮ በክልሉ እየተመናመኑ የሚገኙ አትክልቶችን አልምቶ ለቀጣይ ትውልድ እንዲተላለፍ የሚያስችል ነው።
የዕደ ጥበብ መሸጫ ማዕከላት፣ የመዝናኛ እና የስብሰባ አዳራሾችን በውስጡ ያካተተው የሀረር ኢኮ ቱሪዝም ፓርክ በአካባቢው ለተሰማሩ ወጣቶች የስራ እድል ተጠቃሚነት እንዲጨምር አድርጓል።
ፓርኩ ከተገነባ ወዲህ ወደ ክልሉ የሚመጡ የውጭና የሀገር ውስጥ ጎብኚዎች ቁጥር ትርጉም ባለው መልኩ እንዲጨምር ከማድረጉም በተጨማሪ የጎብኚዎችን ቆይታና ከዘርፉ የሚገኘው ገቢ ማሳደግ አስችሏል።
የሀረር ቀደምት የግንባታ ኪነህንፃ ጥበብን በጠበቀና አምስቱ የሀረር ጁገል መግቢያ በሮችን በሚያሳይ መልኩ እውን ተደርጓል።
ሀረር ላይ ጅብን መመገብ ለበርካታ አመታት የዘለቀ ቢሆንም የሀረር ኢኮ ቱሪዝም ፓርክ ግን ትርዒቱ በአዲስ ምዕራፍና በላቀ ምቾት እየተካሄደ የጎብኚዎች የሀሴት ምንጭና የዘርፉ ተጨማሪ አቅም ሆኗል።