ቀጥታ፡

በጋምቤላ ክልል የሰብአዊ ድጋፎችን በእራስ አቅም ለመሸፈን ለተያዘው ግብ መሳካት  የባለድርሻ አካላት ትብብር ይጠናከራል  

‎ጋምቤላ፤ ነሐሴ 28/2018 (ኢዜአ) ፡-በጋምቤላ ክልል ሰብአዊ ድጋፎችን በራስ አቅም ለመሸፈን ለተያዘው ግብ መሳካት የባለድርሻ አካላት ትብብር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ጋትሉዋክ ሮን (ዶ/ር) ገለጹ።

ተረጅነትን ለማስቀረት እየተከናወኑ ባሉት ስራዎችና  በቀጣይ የበጋ መስኖ የግብርና ልማት ዙሪያ ያተኮረ የንቅናቄ ውይይት መድረክ ዛሬ በጋምቤላ ከተማ ተካሄዷል።


 

ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት፣ ለሚከሰቱ የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ችግሮች ሰብአዊ ድጋፎችን በራስ አቅም ለመሸፈን ባለድርሻ አካላትን ያሳተፉ ተግባራት እየተከናወኑ ይገኛሉ።

በክልሉ ከተረጅነት ወደ ምርታማነት ለመሸጋገር የተቀየሱ እቅዶችን ውጤታማ ለማድረግ ያለውን ሰፊ የመሬትና የውሃ ሀብት ካለው የሰው ኃይል ጋር አቀናጅቶ ለመጠቀም እየተሰራ ይገኛል ነው ያሉት።

በዚህም ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ሉዓላዊነትን ከማረጋገጥ ባለፈ፣ ለሚያጋጥሙ የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ችግሮች በራስ አቅም ሰብአዊ ድጋፍ ለመስጠት የመጠባበቂያ የሰብል ምርትና የበጀት ፈንድ ላይ ትኩረት መሰጠቱን አስረድተዋል።

ምርታማነትን ከማሳደግ ጎን ለጎን ወቅት ጠብቆ ከማምረት ለመውጣት ለተነደፈው የበጋ ወራት የመስኖ ልማት ከወዲሁ አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረግ እንደሚገባም አሳስበዋል።

ለዘርፉ ስኬታማነት በጋራ መረባረብ የሚገባ ሲሆን የግብአትና የባለሙያ ድጋፍ ለአርሶ አደሩ ለማቅረብ  ከመቼውም ጊዜ በላይ መስራት እንደሚገባ ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ አክለው ገልጸዋል።

በክልሉ ሰብአዊ ድጋፎችን በራስ አቅም ምላሽ ለመስጠት የ400 ሚሊዮን ብር የመጠባበቂያ ፈንድ እቅድ ተነድፎ ንቅናቄ መጀመሩንም አስረድተዋል።


 

በብልጽግና ፓርቲ የጋምቤላ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አሸኔ አስቲን በበኩላቸው፣ እንደ ሀገር ከተረጅነት ለመውጣት እየተተገበረ ላለው ኢኒሼቲቭ ውጤታማነት የመንግስትም ሆነ የድርጅቱ አመራሮች በቁርጠኝነት መስራት ይገባል  ብለዋል።

በተለይ ሕብረተሰቡ ምርታማነቱን በማሳደግ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ እንዲችል ያልተቆጠበ የድጋፍና የክትትል ስራዎችን ማከናወን የግድ እንደሚለው ነው የተናገሩት።

በንቅናቄ የውይይት መድረኩ ላይ የመንግስትና የድርጅት አመራሮች እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም