ቀጥታ፡

የአዳማ ከተማ የኢንቨስትመንት ፍሰትን ለማሳደግ የአገልግሎት አሰጣጡን ዲጂታላይዝ አድርጓል

አዳማ ፤ነሐሴ 28/2018(ኢዜአ )፡-የአዳማ ከተማ አስተዳደር የኢንቨስትመንት ፍሰትን ለማሳደግ የመሰረተ ልማትና የአገልግሎት አሰጣጥን  ዲጂታላይዝ ማድረጉን  የአስተዳደሩ ከንቲባ ሃይሉ ጀልዴ ገለፁ።

በከተማዋ በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች የተሰማሩ ባለሃብቶች የተሳተፉበት ፎረም ተካሄዷል ።


 

የአዳማ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ሃይሉ ጀልዴ እንደገለፁት፣ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴን በስፋት ለማሳደግ ከተማ አስተዳደሩ በዋናነት ትኩረት አድርጎ እየሰራ ይገኛል።

የሕዝብ ወይም የተቋማት አገልግሎት አሰጣጥን ይበልጥ ዘመናዊ፣ ፈጣን እና ቀልጣፋ ለማድረግ ዋናው ትኩረት የተደረገው መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ላይ ነው ብለዋል።

በዚህም በከተማዋ ኢንቨስትመንትን በማስፋፋት ለወጣቶች የሥራ ዕድል ለመፍጠር፣ እንዲሁም ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማትን ተደራሽ ለማድረግ በትኩረት እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል።


 

የአዳማ ከተማ ኢንቨስትመንት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ ሐሲያ ኢሳ በበኩላቸው፤ በከተማዋ ኢንቨስትመንትን በማበረታታት ምርቶችን ለውጭ ገበያ ለማቅረብና የተኪ ምርቶችን ለማሳደግ በተደረገው እንቅስቃሴ አበረታች ውጤት መገኘቱን ገልጸዋል።

በዚህም ዘርፉ የግንባታና የፍጆታ ምርቶችን በማምረት ገበያውን ለማረጋጋት በሚደረገው ጥረት ውስጥ የጎላ ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

የአዳማ ከተማ የኢንቨስተሮች ፎረም አስተባባሪ አቶ ፈይሳ አራርሳ በበኩላቸው፤ ፎረሙ በባለሀብቶችና በአስተዳሩ መካከል ያለውን ትስስር በማጠናከር የመሠረተ ልማትና የመሬት አቅርቦት ጥያቄዎችን በትብብር ለመፍታት እየሠራ መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህም የከተማዋን የኢንቨስትመንት ፍሰት ለማሳለጥና የባለሀብቶችን ተሳትፎ ለማጠናከር ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ መሆኑን አስረድተዋል።

ከፎረሙ ተሳታፊዎች መካከል የኩሩፍቱ የወረቀት ፋብሪካ ተወካይ አቶ ሲሳይ ጌታቸው፤ መንግሥት ባለሀብቶች በፍጥነት ወደ ሥራ እንዲገቡ ለማስቻል የኢንቨስትመንት መሬትና የመሠረተ ልማት ጥያቄዎችን በወቅቱ ምላሽ እየሰጠ መሆኑን ገልጸዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም