ቀጥታ፡

በአማራ ክልል የቴክኖሎጂውን ዘርፍ ቁልፍ የእድገት መሳሪያ ለማድረግ እየተሰራ ነው - ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ

ባህርዳር ፤ ነሃሴ 28/2018 (ኢዜአ) ፦ በአማራ ክልል የቴክኖሎጂውን ዘርፍ ቁልፍ የእድገትና የመወዳደሪያ መሳሪያ አድርጎ ለመጠቀም በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አረጋ ከበደ ገለጹ።

በክልሉ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ቢሮ "የኤሌክትሮኒክስ መንግስት የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 መሰረት ነው" በሚል መሪ ቃል የፓናል የውይይት በባህር ዳር ከተማ እየተካሄደ ነው።

ርዕሰ መስተዳደሩ በውይይቱ ላይ እንደገለጹት፣ በክልሉ ፈጠራና ቴክኖሎጂን የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ አቅም ማሳለጫ ለማድረግ እየተሰራ ይገኛል።

በአማራ ክልል "ዲጂታል አማራ" በሚል በ25 ዓመቱ የዕድገት እና ትራንስፎርሜሽን ፍኖተ ካርታ ላይ ቴክኖሎጂ እንደ ልማት መዳረሻ መፍጠሪያ ተደርጎ ተይዟል ብለዋል።

በ25 ዓመቱ ስትራቴጂክ ግብ ላይ በ2042 የአማራ ክልል ዋነኛ ሀብት፤ የአገልግሎት መስጫ እና የኢኮኖሚ የዕድገት ምንጭ ቴክኖሎጂ እንዲሆን ይሠራል ነው ያሉት።

በዚህም ዘርፉን የሚመራውን ተቋም በአዲስ በማደራጀት፣ አሰራሮችን በመዘርጋትና አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ መሰራቱን አስረድተዋል።

በአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ላይ በቴክኖሎጂና ዲጂታላይዜሽን የታገዘ ፈጣን፣ ቀልጣፋና ከብልሹ አሰራር የጸዳ አገልግሎት ለመስጠት ያስቻለ ውጤት መመዝገቡን አስረድተዋል።

በቀጣይም ተቋማት ቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ የማምረትና አገልግሎት የመስጠት ተግባር ላይ አተኩረው እንዲሰሩ አስፈላጊው ድጋፍ እንደሚደረግም አስገንዝበዋል።

የኢፌዴሪ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ(ዶር) በበኩላቸው፣ በቴክኖሎጂና ፈጠራ ላይ በትኩረት በመስራት ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025ን ማሳካት ተችሏል ብለዋል።

ባለፈው አፈጻጻም የተገኘውን ተሞክሮ በመቀመርም አሁን ላይ ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030ን ለማሳካት ዘርፈ ብዙ ተግባራት እየተከናወኑ እንደሚገኙ አስረድተዋል።

የቴክኖሎጂ መሰረተ ልማትን በማሟላት የዲጂታል ግብይት፣ ከወረቀት ንክኪ ነጻ የሆነ የመንግስት አገልግሎትና ጉልበት የቀነሰ አመራረት እውን በማድረግ ለውጥ መመዝገቡንም አስረድተዋል።

ይህም የሰው ኃይሉን በኢትዮ ኮደርስ በማሰልጠን ጭምር በተሰማራበት የስራ ዘርፍ ሁሉ ውጤታማና በዓለም አቀፍ ጭምር ተወዳዳሪ እንዲሆን በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ አስረድተዋል።

በአገራችን የሚገኘው ወጣት ኃይል ራሱን በቴክኖሎጂ እውቀትና ክህሎት በማነጽ እየመጣ ያለውን ዓለም አቀፍ ውድድር ለማሸነፍ መዘጋጀት እንዳለበት አሳስበዋል።

በፓናል ውይይቱ ላይ የፌዴራልና የክልል የዘርፉ አመራሮችና ባለሙያዎች የተሳተፉ ሲሆን በእለቱም የክልሉ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ቢሮ ያዘጋጀው የቴክኖሎጂ ውጤቶች አውደ ርዕይ ለእይታ ክፍት ተደርጓል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም